Wednesday 30 August 2017

የፖለቲካ ባህላችን

አየሽ እዚህ አገር ከንቱ ፍረጃ አለ፤
አማኝ ሁሉ አክራሪ፤
ሙስሊሙ አሸባሪ፤
ጉራጌ ቋጣሪ፡፡
ትግሬ ሁሉ ወያኔ፤
ወጣቱ ወመኔ፡፡
አማራው ነፍጠኛ ፤
ደርግ ሁሉ ግፈኛ፡፡
ናቸው እያስባለ ፤
ቁልቁል የሚነዳን ጭፍን ጥላቻ አለ!፡፡
(ገጣሚ ዮናስ)
*
‹‹አማራ በሙሉ ጨቋኝ፣ ትምክህተኛ እና የድሮ ስርዓት ናፋቂ አይደለም፣ ኦሮሞው ሁሉ ጠባብ እና የኦነግ ተላላኪ አይምሰልህ፣ ትግሬ መሆን ብቻም በህወሓት (ኢህአዴግ) ጠበቃነት አያስወቅስም፤ የኢህአዲግ አባል አለመሆን ደግሞ ፀረ-ሰላም ተብለን በሻዕቢያ ተላላኪነት ተፈርጀን ዶክመንታሪ እንድሰራብን ሊያደርግ ፈፅሞ አይችልም፡፡››

በኢትዮጵያ የፓለቲካ ባህል ኢህአዴግ ካልሆንክ ተቃዋሚ ነህ፡፡ ተቃዋሚ አይደለሁም ካልክ አንተ የኢህአዴግ ቡችላ ወይም ህዋስ ትባላለህ፡፡ መሀል ላይ ቆመህ የምክንያት ሰው ነኝ ከማንም ጋር የስሜት ቁርኝት የለኝም በማለት የማንም ጠበቃ አልሆንም ኢህአዲግ ሲያጠፋ ከመውቀስ አልመለስም፤ ተቃዋሚዎችም የተሳሳተ ነገር ሲሰሩ እተቻለሁ ብለህ በአቋምህ ብትፀና መሀል ሰፋሪ በሁለት ጥይት ይመታል እንዲሉ ከሁለቱም በኩል ተኩሰው ይመቱሀል፡፡ ምናልባት ከጥቃቱ ተርፈህ ከሆነም ሳትወድ በግድ ፅንፈኛ አቋም እንድትይዝ ጫና ይደረግብሀል፡፡ ለምን ካልከኝ ምክንያቱ ያለኸው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ፓለቲካ በስሜታውያን ፊትአውራሪነት የሚመራ ይመስላል፡፡ ልብ ብሎ ላስተዋለ በአመክንዮ ከሚመሩን ፖለቲከኞች ይልቅ በእውር ድንብሩ የሚጓዙት የስሜት ፈረሰኞችና አስጋላቢዎች ይበልጣሉ፡፡
ማህበረሰባችንም በባህሪው ፅንፈኛ ነው፡፡ ሁለት የአስተሳሰብ ጎራዎች አሉ፡፡ ከነሱ መውጣት አይፈቀድልህም፡፡ ከዚህ ውጭ እሆናለሁ ካልክ በሁለቱም ወገን ትወገዛለህ፡፡

ኢትዮጵያዊ ነኝ አማራ፣ ኦሮሞ ፣ ትግሬ ፣ ደቡብ፣ አፋር ፣ ሱማሌ ፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ወዘተ አይደለሁም ብትል ደግሞ ሁሉም አሽቀንጥረው ሜዳ ላይ ይጥሉሀል፡፡ ወፍ ዘራሽ ተብለህ ተቆርቋሪ፣ ጧሪና ቀባሪ ታጣለህ ማለት ነው፡፡ ይህ ሁሉ የኢትዮጵያ ወቅታዊ የፓለቲካ ናዳ ነው፡፡ ዘረኝነት ስሩን የሰደደበት ፓለቲካችን አገራዊ ስሜትን መሸርሸር ጀምሯል፡፡ ይህ ብቻ አይበቃቸውም! ኢትዮጵያዊነት ደሜ ነው ብለህ ስትዘምር ደምህን ለማፍሰስ አሰፍሰፈው ይመጡብሀል፡፡ አንዱን ፊት ለፊት ስትጋፈጥ ሌለኛው ጥቃት ያደርስብሀል፡፡ የፓለቲካ ባህላችን በወዳጅነትና ጠላትነት ላይ የተመሰረተ ነውና ጥቃቱን መቋቋም አቅቶህ ፅንፍ ልያዝ ብትልም ጥላቻው አይለቅህም፡፡ ወይ ከኛ አልያም ከነሱ አይነት ባህሪ የፖለቲካ ጨዎታችን መገለጫ ነው፡፡ መሐል ላይ ብትሰፍር በግራም በቀኝም የመከራ ጥፊ ትቀምሳለህ፡፡ ሳትወድ በግድ ጥግ መያዝ አለብህ፡፡

የእኔ የምትለው ድርጅት ችግር ካለበት መተቸት ግድ ይልሀል፡፡ ካልሆነ ግን ለውድቀቱ እየሰራህ መሆኑን አትዘንጋ፡፡ እኛም መከተል ያለብን ድርጅቶችን ብቻ ሳይሆን እውነትን፣ ነፃነትና ፍትህን ነው፡፡ አንተን ያቀፈህ ድርጅት ህዝባዊነት ከሌለው ራስህን መነጠል ታላቅነት እንጅ ቂልነት አይደለም፡፡ የእነርሱ የምትለው ድርጅት መልካም ነገር ከሰራ ድጋፍ ብታደርግ አዋቂነት ነው፡፡ ስለዚህ መሀል ላይ ሁን፡፡ በነፈሰት አብረህ አትንፈስ፡፡ ስማኝ ወገኔ! ፅንፈኛ አትሁን፡፡ አርስቶትል ‹‹ወርቃማው አማካይ›› የሚለው ሌላ አስተምህሮ አለው፡፡ ወርቃማው አማካይ ላይ መሆን ቅቡልነትን እና ትክክለኛ ስብዕናን መወከሉንም ልብ ይሏል፡፡ ስለዚህ እኔ የምልህ ፍልስፍናዊ መሰረት ያለው ነው፡፡ ውኃ የማይቋጥር አሉባልታ አይምሰልህ፡፡ ሁሉም ነገር በመጠኑ ሲሆን ጥሩ ነውና ጫፍ ላይ አትመሽግ፡፡ የሁለቱንም ፅንፍ ምንነት ተገንዝበህ አመዛዝነህ መሀል ላይ ስፈር (ወርቃማው አማካይን መፈለግህን አትርሳ)፡፡ ቀይ ካልሆነ ጥቁር ነው አትበል፡፡

የኛ ማህበረሰብ በሎጅክ ላይ ተመስርተህ ስህተቱን ከምትነግረው ይልቅ ጥቃቅን ስኬቱን አንስተህ ብታሞግሰውና ብታወድሰው ይመርጣል፡፡ ማህበረሰባችን የሚፈጥራቸው የፖለቲካ ድርጅቶችም ከዚህ ልማድ እስር አልተፈቱም፡፡ ቡድንተኝነት መገለጫቸው ነው፡፡ ልማታዊ ድሞክራት ነኝ ለሚል ድርጅት ኒዮ-ሊበራሊዝም ጭራቅ መስሎ ይታየዋል፡፡ ዜጎቹን የኒዮ-ሊበራል አቀንቃኝ እያለም መውጫና መግቢያ ያሳጣል፡፡ ‹‹ከመጠምጠም መማር ይቅደም›› እንዳሉት አፄ ቴዎድሮስ ኒዮ-ሊበራል ብሎ ሰዎችን ከማሳቀቃችን በፊት ስለ ርዕተዓለሙ ጥልቅ እውቀት ሊኖረን ይገባል፡፡ ይህን ያልኩት አንዳንድ ደናቁርት ካድሬዎች ኔዮ-ሊበራሊዝምን ‹‹ውጉዝ ከመአርዮስ›› እያሉ በጭፍን ሲተቹና ሲያወግዙ በማስተዋሌ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ልማታዊ መንግስትን አለመገደፍ የኔዮ-ሊበራል ታፔላ አስለጥፎ ከርቸሌ የሚያስወርድበት ፖለቲካዊ እንቆቅልሽ አልገባህ ብሎኛል፡፡

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል አዳምና ሄዋን በሰሩት ስህተት የሰው ዘር በሙሉ የቅጣቱ ሰለባ እንደሆነው ግለሰቦች ባጠፉትና በእነሱ ሀጥያት ቡድኖች የመከራ ገፈት ሲቀምሱ ማየታችን የተለመደ ነው፡፡ ልክ እንደነ አዳም ታሪክ የኛም የጎሳ ፖለቲካ ‹‹አንድ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ…ወዘተ ባጠፋው ጥፋት ሚሊዮኖች ዋጋ እንድከፍሉ እያስገደደ ነው፡፡›› አንዳንዴ በኦሪት ህግ የሚመራ ረጅም የፓለቲካ ጉዞ የጀመርን ይመስለኛል፡፡ ለመሆኑ ‹‹የአባት እዳ ለልጅ የእማየን ለአባየ አይነት የፖለቲካ ጫወታ ያዋጣን ይሆን?›› እኔስ እልሀለሁ አያዋጣንም፡፡ ‹‹በላይነህ በሰራው ስህተት ደመላሽ መቀጣት የለበትም፤ ኃጎስ በፈጠረው ችግር ገብረእግዚዓብሄር ሊጠየቅ አይገባም፤ መገርሳ ባጠፋው ዱጋሳ አይወቀስም ሊወቀስም አይገባም፡፡›› በወንጀለኛ መቅጫ ህግም የወንጀል ድርጊት ተጠያቂነት በዝምድና ብቻ ከአንዱ ወደ ሌላ አካል ፈፅሞ አይተላለፍም፡፡ በፖለቲካው ዓለም በጅምላ መወንጀሉ መቅረት ያለበት ህጋዊና ሞራላዊ መሰረት ስለሌለው ነው፡፡ የችግሩ ፈጣሪ እስካልሆን ድረስ ‹‹ከኑግ ጋር የተገኘሽ መጭ አብረሽ ተወቀጭ›› በሚለው እሳቤ የሌለብንን እዳ ልንከፍልም አይገባም፡፡ ማንም ሰው በስማበለው የአጥፊው ወገን ስለሆነ ባልሰራው ወንጀል በመሰለኝና በደስአለኝ መንገድ በመሄድ መቀጣት የለበትም፡፡

የመንጋ አስተሳሰብ የትስ ያደርሰን ይሆን? አላቅም! እኔ ካጠፋሁ ተወቃሹ እኔና እኔ ብቻ ነኝ፡፡ በእኔ ወንጀል ማንም ሰው ሊከሰስ አይገባውም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚያሳዝን ሁኔታ ግለሰቦች በመንጋ ጭንቅላት የሚያስቡት ወደው አይመስለኝም፡፡ ተገደው ነው ፤ ለደህንነታቸው ሲሉ! መሀል ላይ ቢሰፍሩ የሚደርስባቸውን ጫና ያውቁታልና ፅንፍ ይይዛሉ፡፡ ለሶስተኛው አማራጭ ብሎም ለግለሰቦች ልዕልና ቦታ ከሰጠን ግን የፓለቲካ ደዌውም ይለቀናል፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ ሰዎች ደጋፊዎቻችን ካልሆኑ ለምን ለኔ አታጨበጭቡም ብለን በጠላትነት እንፈርጃቸዋለን፡፡ ፍረጃው ግን መሰረተ ቢስ ነው፡፡ ለኛም መሻሻል አይጠቅምም፡፡
እኛ አገር የተሻለ ሀሳብን ሳይሆን ቡድኖችን እንድትከተል ትገደዳለህ፡፡ ይህ አካሄድ እውነትን መጨቆን ነው፡፡ ሁሉም ነገር ከምክንያት ይልቅ በስሜት መነፅር መታየት ይጀምራል፡፡ ነገር ግን ምንም ለውጥ አያመጣም፡፡

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ መሀል ሰፋሪዎች ቦታ ቢሰጣቸው ጫፍና ጫፍ ቆመው የተፋጠጡትን ወገኖች በመጠኑም ቢሆን ማስተካከል ይቻል ነበር…ባይሰበር፡፡ መሀል ላይ አስታራቂና ከስሜት የራቀ አካል ከሌለ ተያይዞ የፖለቲካ ሲዖል ውስጥ መግባት ነው፡፡ አጥፍቶ የመጥፋት ፖለቲካ ማለትም ይህ ነው፡፡ ከነችግራችን ልንደገፍ ይገባል ማለት ከችግሩ መውጣት ብሎም ችግሩን ማወቅ አንፈልግም ብሎ ማሰብ ነው፡፡ ሰው ስራ ሲሰራ ይሳሳታል፣ ስህተቴን ለምን ነገራችሁኝ ብሎ ዘራፍ ማለት ግን ከሰውኛ ማንነት መውረድ ነው፡፡ ለለውጥ ከተነሳን አጨብጫቢ ብቻ ሳይሆን የሚተቸን አካል ያስፈልገናል፡፡
አንድ ከብርሃኑ ሞላ ነጠላ ዜማ ላይ የሰማኃት የግጥም ስንኝ ሁኔታውን የበለጠ ስለገለፀችልኝ እንካችሁ ብያለሁ፡፡
አንድ ሰው በአንድ አገር ሲኖር ብቻውን፤
ሳያውቀው ይኖራል የገዛ ነውሩን፡፡
ነውሬን የሚነግረኝ አንድ ወንድም አጥቼ፤
በአመቱ አገኘሁት ለፍቼ ታክቼ፡፡

ስሜታዊነት የኢትዮጵያ ፖለቲካ አልፋና ኦሜጋ መሆኑን ለማወቅ መሀል ሰፋሪዎች ይዞታ ማጣታቸውንና የብዙዎቻችን ነፍስ በዘረኝነት መስከሯን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ለካ ዘረኝነት ልኩን ሲያልፍ ነፍስንም ሳይቀር ያሰክራል፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ያውም ሉላዊነት (Globalization) አለምን ወደ አንድ መንደር ለመጠቅለልና ግሎባል ዜግነት ያለው ትውልድ ለመፍጠር ዳር ዳር እያለ ባለበት ወቅት ኢትዮጵያውያን ከጎሳ ዘንቢል መውጣት አለመቻላችን እጅጉን ያስቆጫል፡፡ ወደድንም ጠላንም እኛ እርስበርስ ስንናከስ ዓለም በጠንካራ የኢኮኖሚ ክንዷ ገፍታ ከጫወታ ውጭ ታደርገናለች ፤ አድርጋናለችም፡፡ የፉክክር በራፍ ሳይዘጋ ያድራል ማለት ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡

እዚህም እዚያም በዘረኝነት የሰከሩ ነፍሶች ሲራወጡ ማየት ተስፋ ያስቆርጣል፡፡ በዘረኝነት የሰከሩ ነፍሶች ሳያጠፉ አይጠፉም፡፡ ዘረኝነት ነፍስን በካይ ጋዝ ነው፡፡ ዘላለማዊነት ያላትን ነፍስ ስሜት ሲያኮላሽብህ ቆመህ ማየት የለብህም፤ ከራስህ ጋር ታግለህ ስሜትን ድል መንሳት ይኖርብሀል፡፡ የስሜት ፈረሰኞችንም በፅናት ልትታገል ይገባል፡፡ ወገኔ ‹‹ነፍስህን አታቆሽሽ›› አደራ! መሪዎች ያልፋሉ የጥላቻ መርዛቸው ግን ይቅር ባይ ልብ ከሌለን አብሮን ይዘልቃል፡፡ እንደ ጎርፍ የሚያልፉት መሪዎች የጥላቻ ደለላቸው እንዳይውጠን በመከላከል ራሳችንን መታደግ ያለብን እኛው ነን፡፡

ህዝብ ለህዝብ በጥላቻ መስኮት እያጮለቀ እንድተያይ ማድረግ ታሪክ በመጥፎ ምዕራፍ እንድያስታውሰን መፍቀድ ነው፡፡ አሁን ያለው የአገራችን ፓለቲካ አንዱ በሌላው ላይ ተነስቶ አንገት የሚቀነጥስበትን ሰይፍ ያዘጋጀልን ይመስላል፡፡ የሚመሩን አካላት ፍቅርን ወደ ጎን ትተው በጥላቻ መንገድ መጓዝ ከጀመሩ ሰፊው ህዝብ በነፈሰበት ስለሚነፍስ ላንመለስ ወደ ጨለማው ሄደን እንቀራለን፡፡ የህዝቡ ንቃተ ህሊና የተሻለ ካልሆነ ውቃው ደብልቀው ሲባል አብሮ መጨፈሩ አይቀርም፡፡

ብሄራዊ መግባባትን መፍጠርና አንድነትን ማምጣት ከባድ የፖለቲካ አሳይመንት ነው፤ የጥላቻ መርዝን መርጨት ግን በጣም ቀላል ነው፡፡ ደካሞች ጥላቻን ሲዘሩ ተባባሪዎቻቸው አጭደው ይወቃሉ፤ ጠንካራና እውነተኛ የህዝብ ልጆች ግን ለፍቅርና አንድነት ይሰራሉ፡፡ ደናቁርት ዘረኛ ሲሆኑ የበሰሉትና ምክንያታዊ የሆኑት ግን የአንድነት ዜማን ያዜማሉ፡፡ ቁሳዉያን ዘረኝነትን ሲያነግሱ መንፈሳዉያን አንድነትን ይሰብካሉ፡፡ ለሆዱ ያደረ ባለስልጣን ህዝብን ሲከፋፍል፤ እውነተኛ ህዝባዊነት ያለው ግን የዘረኝነት እሳት ላይ የአንድነት ውኃ ይቸልሳል፡፡ የተማረው መሀይም ጠባብ ሲሆን የእውቀት አዝመራን የወቃው ግን ከአገርም አልፎ ለአለም ይጨነቃል፡፡

‹‹ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል ሁሌም እንደደማ ይኖራል›› እንድሉ ከዘረኞች ጋር ለመኖር ዘረኛ መሆን ግደታ ሆኖ ሲመጣብህ የሞቀ አቀባበል ካላደረክ የፅንፈኞች ጥቃት ሰለባ ትሆናለህ፡፡ መግቢያና መውጫም ያሳጡሀል፤ ቢሆንም! እመነኝ! ዘረኛ ሆኖ ከመገኘት በዘረኞች የጥላቻ ብትር መደብደብና መሰቃየት ይሻላል፡፡ እነሱ ቢያሰቃዩህ ስጋህን ቢጎዱት እንጅ ነፍስህ ምንም አትሆንም፡፡ አንተ ብትደማ፣ ብትቆስልና ብትቆሽሽ ነፍስህ ንፅህት ናት፡፡

ሁሌም ኢትዮጵያዊነቴ አለፍ ሲልም ሰው መሆኔ እንጅ የመጣሁበት ክልል ለኔ ምኔም አይደለም፡፡ አማራው ሲበደል ያመኛል፣ ኦሮሞው ጥቃት ሲደርስበት ህመሙ ይሰማኛል፣ ትግሬና ደቡቡ፣ አፋሩና ሱማሌው፣ ቤኒሻንጉሉ እና ጋምቤላው እንድሁም ከሐረር የመጣው ሲከፋው አብሮ ይከፋኛል፣ እንቅልፍም ይነሳኛል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም! ድንበር ዘለል የሆኑ የሰው ልጅ ስቃዮች ያሳስቡኛል፡፡ እዚህ ሁኜ መካከለኛው ምስራቅ ያለው ብጥብጥ ሰላሜን ይነሳኛል፡፡ እኔ ስለ መካከለኛው ምስራቅ ቀውስ አላስብም ብየ እንኳን ባስብ አለማሰቤ ቀስቅሶ ያሳስበኛል፡፡ ለምን ብለህ ከጠየከኝ እነሱም በአንድየ አምሳል የተፈጠሩ ሰዎች ናቸው የሚል ምላሽ አዘጋጅቸልሀለሁ፡፡ ዘር ለገበሬ ነው ሲሉ ሰምተህ ከሆነ ያልኩት ይገባሀል፡፡ የሰው ልጅ አንድ እንጅ የተለያየ ዘር የለውም፡፡ በመልክና በባህርይ ብንለያይ እንኳን ደማችን አንድ ነው፡፡ ነጭ ደም ያለው ካለ እኔ ደሜ ቀይ ነውና አሁኑኑ ዘረኛ እሆናለሁ፡፡
በዘረኝነት መርዝ የተለወሰ ፅንፈኛ የሆነ ጥላቻ አዘል ፖለቲካ አገርን ያፈርሳልና በእስካሁኑ ይብቃን፡፡

የማንነት ጥያቄ መጥምቁ ዮሀንስ (ዋለልኝ መኮንን ካሳ)


የታሪኩ መግቢያ (ተከታታይ ትረካ ነው)

(በ Derbe Tefera)

‹‹ከለበሱ አይቀር ሱሪ፤
የጥንቱን ነበር የተፈሪ፡፡
ግና አይመችም ለስራ፤
አጣብቆ ይዞኝ በቀኝ ግራ፡፡››
ቅኔው የዋለልኝ ነው፡፡

2007 አመተ ምህረት ነበር ስለ ዋለልኝ መፅሀፍ ላዘጋጅ የተነሳሁት፡፡ ከዛን ጊዜ ጀምሬ ስለ ፓለቲካ ህይወቱ እና እይታዎቹ መረጃዎችን ሳፈላግል ብሎም አስተዳደጉን በተመለከተ የቅርብ ዘመዶቹን እየፈለኩ ቃለ መጠይቅ ሳደርግ ቆየሁ፡፡ ቃለመጠይቅ ካደረኩላቸው ግለሰቦች መካከል የዋለልኝ ዘመድ የሆኑት ዶክተር አየለ ታረቀኝ ይገኙበታል፡፡ ዘግይቸ ከመፅሀፉ ይልቅ አርቲክል ይሻላል የሚል ሀሳብ መጣልኝና ስራየን ቀጠልኩ፡፡ በስተመጨረሻም የምፈልጋቸውን መረጃዎች አግኝቸ ስራየን ወደማጠናቀቁ ተቃረብሁ፡፡

ለመወያየት ያመች ዘንድ ከአርቲክሉ ቀንጨብ እያረኩ ለእናንተም በተከታታይ ክፍል ለማቅረብ ወስኛለሁ፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ቅድመ ታሪክ ሀተታውን ለመግቢያ ያክል እነሆ ብያለሁ፡፡
ዋለልኝ እንደ መጥምቁ፦ ያው እንግድህ ዮሀንስ በዮርዳኖስ ወንዝ በሚያጠምቅበት ወቅት ፈጣሪ መጥቶ፡- ‹‹አጥምቀኝ›› ሲለው ዩሀንስ ‹‹እኔ ባንተ መጠመቅ ሲገባኝ እንዴት አንተን አጠምቃለሁ አለው?›› ፈጣሪም ‹‹ሌሎች የኔን ፈለግ ተከትለው ሳይጠራጠሩ እንድጠመቁ እንድሁም ትህትናን ይማሩ ዘንድ እኔን አጥምቀኝ ከዛ ህዝቡ ተከትሎ ይጠመቃል›› ብሎ መለሰለት፡፡ ዩሀንስም በፈጣሪ መጠመቅ ሲችል እርሱ ፈጣሪውን አጠመቀ፡፡ ይህን ተከትሎም ለመጠመቅ ያለው ፍላጎት ጨመረ፡፡ ፈጣሪ ሲጠመቅም ተዓምር ታየ፡፡
.
ዩሀንስ ‹‹እኔ በውሃ አጠምቃችኋለሁ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን በእሳት ያጠምቃችኋል›› ሲል ተናገሮም ነበር፡፡
አሁን እናንተ እንድትይዙልኝ የምፈልጋቸው ሁለት ነገሮች አሉ፡፡ አንደኛው ሌሎች እንድጠመቁ በምን መልኩ አምነው ተገፋፉ የሚለው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከጌታ መጠመቅ በኋላ ምን ተፈጠረ የሚል ነው፡፡

ወደ ማንነት ፖለቲካው አጥማቂ ስንመጣ ብዙ ተከታይ ማፍራቱን ልብ ይሏል፡፡ በወቅቱ የማንነት ጥያቄን ተጨቁነናል ብለው የሚያስቡት ቡድኖች ማንሳት ሲችሉ የማንነት ፖለቲካው አጥማቂም ራሱ በወቅቱ ተጠቃሚ ናቸው ተብለው ከሚታሙት ወገን ቢሆንም ቅሉ ጉዳዩ ይመለከተኛል በማለት ጥያቄውን አንስቶ ለተቀሩት ተከታዮቹ የማንነት ፖለቲካን በማንሳት በውስጣቸው ያለውን ስሜት እንድተነፍሱ በማስቻል ለማንነታቸው ዘብ ይቆሙ ዘንድ በራሱ አንደበትና የሃሳብ ጉልበት ብዕሩን ተጠቅሞ በሩን ከፈተላቸው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ይህ አቋም ግን ትክክለኛነቱ መፈተሽ አለበት፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ጨቋኝ እና ተጨቋኝ አለ ወይ የሚለው ሀሳብ በራሱ አከራካሪ ነው፡፡
ልክ ዮሀንስ ‹‹ከእኔ የበለጠ አጥማቂ ይመጣል›› እንዳለው ፖለቲከኛውም፡- ‹‹እኔ የማንነት ፖለቲካን በማርክሲስት ሌኒኒስት ውሀ አጠምቃችኋለሁ ከእኔ በኋላ የሚመጡት ግን በአብዮታዊ ድሞክራሲ እሳት ይጠምቋችኋል›› ያለም ይመስላል፡፡ (እዚህ ላይ እሳት ስል ዮሀንስ እንዳለው መንፈስ ቅዱስን ማለቴ አይደለም) ፡፡
.
በአስገራሚ ሁኔታ የጌታ መጠመቅን ተከትሎ የዮርዳኖስ ባህር እንደተከፈለው የማንነት ፖለቲካ አጥማቂውም ጉዳዩን ባነሳው ወቅት የአንድነት መንገዱ እንደ ቻይና አስፋልት ተሰንጥቆ የማንነት መስመሮች መሰመራቸው አልቀረም ነበር፡፡ በዚህ የተነሳም ብዙ ውዝግቦች ተፈጠሩ፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው በወቅቱ እንደ ታቦ ይቆጠር የነበረውን የብሄረሰቦች ጉዳይ የሚዳስስ ፅሁፍ የያኔው የቀዳማዊ ሐይለ ስላሴ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ልሳን በሆነችው ታገል መፅሄት ላይ ‹‹የብሄረሰቦች ጥያቄ በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ ታትሞ ለአንባቢ ይፋ መሆኑን ተከትሎ እንደሆነ ብዙዎች ይመሰክራሉ፡፡ ይህ ማለት ግን ፅሁፉ ከመውጣቱ በፊት ማንነትን ያነገቡ እንቅስቃሴዎች አልነበሩም ማለት ሊሆን አይችልም፡፡ የንጉሱን ስርዓት በመቃወም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ይካሄዱ የነበሩ አመፆችም ማንነትን የተመለተ አንድምታ እንደነበራቸው የሚካድ አይደለም፡፡ ይህ በእንድህ እንዳለ የብሄረሰቦች ጥያቄ ምላሽ ሊሰጥ ይገባዋል የሚል አቋም በይፋ የትግሉ አንዱ አካል መሆኑ ለይቶ የወጣው የፖለቲከኛው መጥምቁን ፅሁፍ ተከትሎ ነው የሚል እምነት በብዙዎች ዘንድ ይስተዋላል፡፡
.
ስለ ዋለልኝ ሲነሳ በአንድ በኩል የነፃነት ፋኖ ወጊ እና አርበኛ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ከዚህ የተለየ እሳቤ አላቸው፡፡ ‹‹የበላበትን ወጭት ሰባሪ፤ ለጥላቻ ተወልዶ አገርን በመከፋፈል ያደገና ኢትዮጵያን ከማትወጣበት የፖለቲካ አዘቅት ውስጥ ጨምሮ ያለፈ ብለው ይፈርጁታል፡፡›› የአስገንጣይነት ካባም የተሰጠው ለዋለልኝ ይመስላል፡፡ ዋለልኝ መኮንን እንደ ከፋፋይ፣ አስገንጣይ፣ የጥላቻ ፖለቲካ ቀመር አዘጋጅ፤ ይህም ሳያንሰው የአጥፍቶ መጥፋት የፖለቲካ መንገድ ቀያሽ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ እራሱ አማራ ሆኖ አማራን ነጥሎ እንደ ጨቋኝ አድርጎ ለማቅረብ የሞከረበት አግባብም ከእውነት የራቀ ነው የሚሉ ወቀሳዎች ይሰነዘራሉ፡ የአስገንጣይና ከፋፋይነት ካባው ይስፋው ወይም ይጥበበው ኋላ ላይ የምናየው ይሆናል፡፡ መቼም የልጅ ጃኬት ለአባት፤ የአባት ደግሞ ለልጅ እንደማይሆን ግልፅ ነውና በተመመሳሳይ ለዋለልኝ የተሰፋለት የፖለቲካ ካባ ልክ ሊሆንም ላይሆንም ይችላል የሚል እሳቤ ሊኖር ግድ ነው፡፡ በሶስተኛ ደረጃ የምናገኛቸው ወገኖች በበኩላቸው ስለ ዋለልኝ መኮንን የራሳቸውን ሃሳብ ሰንዝረዋል፡፡ በእነሱ አረዳድ ዋለልኝ ያነሳው ነገር በነውርነት የሚፈረጅ አይደለም፡፡ ሀሳቡም ቅድስናን የተላበሰ ሊሆን ፈፅሞ አይችልም፡፡
ለግንዛቤ ይረዳ ዘንድ በ ታገል (Struggle) መፅሔት ላይ ከታተመችውና ለመጀመሪያ ጊዜ አይነኬ ስለነበረው የብሄር ጥያቄ ዋለልኝ ከከተባት ፅሁፍ ወሳኝ ነጥቦችን በመውሰድ ዘርዘር አድርገን በሚቀጥሉት ቀናት የምንወያይበት ይሆናል፡፡

Tuesday 29 August 2017

መልካም አገዳደል ወይስ መልካም አስተዳደር?


(በ መሳይ እስከዳር አበራ)

     ባልጠበኩት በተረገመ ባልተጠራ አንድ ቀን ለምድር የከበደ ዝናብ ጣለ የደሀ ጎጆዬን ጎርፍ አባ ሳሙኤል ግድብ ጠቅልሎ ሳይከታት ለማትረፍ የጣራዬን ቀዳዳ ለመድፈን ብጥር ይባስ እየከፈትኩለት ቤቴን ደጅ አድርጌው ቁጭ አልኩ! ጠብ ሲል ስደፍን ጠብ ሲል ስደፍን እንዲሁ ሌሊቱን አደርኩ

     የቤቴን ክዳን ቆርቆሮ ላስተካክል ሳስብ ገና ለ ገና ከየት መጣ ያልተባለ መጥሪያ እጄ ላይ ደረሰ!… …ገና ለገና ዛሬ ጣሪያው አፈሰሰና ነገ ጣራ ሊቀይር ይችላል ተብሎ የጠቆመው ማን ይሆን?? እያልኩ ሳሰላስል… ………መቼም ሰው ሳይሆን ባለ አውሊያ ጠንቆይ መሆን አለበት ይህን መረጃ ለወረዳው ያቀበለው……በቃ የኛ ሰፈር ጠንቋይ ሳይቀር ተጠሪነቱ ለቀበሌ ሆኖ ይቅር ዘንድሮ ምን ተሻለን?  ……… ጠንቋዩም… ለሰይጣን ትቶ ለመንግስት አደረ  ማለት ነው? !……… እረ ደግ አደረገ እያልኩ ከማያውቁት መላአክ የሚያውቁት ሰይጣን ይሻላል ብዬ …በዚህ ስገረም ዋልኩ!……አሁን ነገ በለሊት ተነስቼ ጣራውን መቀየር አለብኝ ብዬ የተማከርኩት ከራሴ ጋር ነበር ለነዚህ ጠንቋዬች ስራ ደርቦ መስራት ምን ፋይዳ ይኖረው ይሆን? እየገረሙኝ  አይ መጨካከን ብዬ ወደ ተጠራሁበት ቢሮ አቀናሁ!

     ኧረ የሰው ጆሮ ግን በጣም ተሻሽሉዋል ጆሮው ከአፍ ሳይሆን ከልብ መስማት እና ማዳመጥ ጀምሯል ይሄ የአምስት አመቱ የትራንስፎርሜሽን እቅድ ውስጥ ይካተት አይካተት የማውቀው ነገር የለም! ግን እውነት እውነት እልሀለው ከራሴ በቀር ይሄን ቆርቆሮ ስለማስተካከል ያወራሁት አንድም ሰው አልነበረም አዕምሮየ እንኳን ይሄን ሲያስብ ኪሴ ይሄን ደባ አያቅም ነበር! ደሞዜ ከምፅአት ቀን አንድ ቀን ቀደም ብሎ እስኪመስለኝ ድረስ እሩቅ ነበር! ደሞዝ ከተባለ የመንግስት ደሞዝ የወንድ ልጅ ፔሬድ ነው ስለተባለ ከደሞዝ አልቆጥረውም!

     ጠሩኝ አደል? በሰአቱ ተነስቼ ወደ ወረዳው አመራሁ!
ገና የቁርስ ሰአት ቢሆንም የደንብ ስራ ሂደት ሀላፊው እኔ ስደርስ ምሳ ወተዋል

     እናት ገና እኮ ነው ሰአቱን እይው እስቲ ሁለት ተኩል ነው ስላት?… አንድ ፀሀፊያቸው ትሁን አፀያፊያቸው ትሁን በውል ያልገባችኝ እንስት በአይንዋ ፊቴን ሞነጫጨረችው… አይ በቃ እንግዲያው ስኳር ይኖርባቸው ይሆናል ለዚህ ነው እየበሉ የሚርባቸው ብዬ ወጣሁ!………በመብላት እረገድ የሚደረገውን ጥረት ለአገልግሎት ጥራት ቢደረግ ምንኛ ደግ ነበር! ልል ፈልጌ የፀረ ሽብር ህጉን አስታውሼ አፌን ለጎምኩ!

     ደንብ ለማክበር ደንብ የማይከበርበት ሀገር ላይ መኖሬ የሚያሳዝነኝ አንድ ወቅት ላይ  ቀለም ስትቀባ መተህ ማስፈቀድ አለብህ ተብሎ የቤቱ ግርግዳ  ቀለም በደንብ ማስከበር የስራ ሂደት ሃላፊው አማካኝነት  የተፈቀፈቀበት ሰው ስለማውቅ ነው!

  አንዴ ደሞ   የቤቱ ቁልፍ ጠፍቶት ለመቀየር የፈለገው ግለሰብ ወረዳ ድረስ መተህ በራፖር አመልክተህ የቁልፉን ቀዳዳ እንደማታሰፋው ቃል በመግባት ፈርም የተባለ ግለሰብ ስለማውቅ ነው!

     ያሳያቹ…እኔ አድሳለው ያልኩት አፍርሼ አልነበረም አፍርሶ የመገንባት አቅሙም ጉልበቱም አልነበረኝም ሀሳቤ ይፈሳል ያልኩበትን ቦታ ወቶ መለጠፍ ነበር ብዙ ቦታ ስለምለጥፍ አዲስ የመጣ ቆርቆሮ መስሉዋቸው ቤቴን እንደ ጆፌ አሞራ ሊከብዋት ስለሚችሉ ነበር አስቀድሜ ጥሪዬን አክብሬ ቢሮ የተገኝሁት!

     ለማንኛውም ጠሪ አክባሪ ነው ብዬ ነበር የሄድኩት… እግሬን ወደ ቀበሌ ከማነሳ ሞቴን እመርጥ የነበርኩ ሰው እኮ ነኝ ዛሬ ግን የህግ መጥሪያ ሲደርሰኝ ምን ላድርግ ወደ ወረዳው አቀናሁ፡፡

     መቼ ነው? ስለኔ መጨነቅ የማትሰለቸው የሚለዉን ዘፈን እኔ መቼ ነው ስለኔ መጨነቅ ምትጀምረው? አያልኩ ገልብጬ በመዝፈን ያቀናሁት !…………በቃ እራት ብለው ሳይወጡ መክሰስ ላይ ወይ ምሳ ላይ  እመጣለው ብዬ አፀያፊዋን  ተሰናብቼ ወጣሁ።

     እኔ የሚገርመኝ የትም አይሄዱም  ለመስክ ስራ ይወጡና አስከ ሶስተኛ አንዱ ህገወጥ ግንባታ የገነባ ልማታዊ ሌባ ጋር ገብተው ጃንቦ አክትመው ይወጣሉ፡፡

      ሌላው በየ ህንፃ መሳሪያው መደብር ሰላይ ወይም ስኩፒኒ አስተኩኣሽ ያስቀምጣሉ ማን ቆርቆሮ ገዛ ማን ሚስማር አስላከ ተቀምጠው በአይነ ቁራኛ ይከታተላሉ አንተ ሀገር አማን ብለህ ኪሎ ኮፍያ ሚስማርህን ይዘህ ስትገባ በጎን እንደኔ መጥሪያ ይደርስሀል በቃ እንደትራፊክ እየተከታተሉ ኑሮህን እንዳታሻሽል ቤትህን እንዳታሳምር ቁም ስቅልህን በቅጣት እና የካብከውን በመናድ እንዲሁም በማፍረስ ፍዳህን ያሳዩሀል! አንድም ቀን ህገ ወጥ የተባለ ፎቅ ሲፈርስ አላጋጠመኝም ሁሌ የምስኪን ደሀ በዩኒሴፍ ድንኮን የተሰራ ጣራ ከንፋስ ተርፋ በደንቦች ስትገነጣጠል ማየት የሰርክ ተግባሬ ነው።

     ሌላው የሚገርመኝ የደንብ ስራ ሂደት ባለቤቱ ባለስልጣን ሳይሆን፣ የሊቀመንበሩ ነው ቢሮአቸው እላይ 5ተኛው ፎቅ ላይ ነው…ያው የሚገባው ይገባዋል ለምን እዛ እንደተሰቀሉ፡፡ እኛን አትደረሱብን ለማለት ነው፡፡ ልሰማችሁም ልረዳችሁም ላናግራችሁም ችግራችሁንም ልካፈል አንፈልግም ነው፡፡ ግልፅ አኮ ነው እሳቸው ከኛ ግብር እና ታክስ ተቆርጦ የሚከፈላቸውን ደሞዝ ብቻ ነው የሚፈልጉት !

     የትኛው አካል ጉዳተኛ ነው በዊልቸር ወቶ ችግሩን በአካል የሚያስረዳው? ያሳያቹ አሁን የዘጠና አመትዋ እማማ ናቸው ወይስ አባባ ናቸው በትኩሱ ጉልበታቸው እላይ ታች የሚሉለት ቀበሌ ጉዳይ ከማስፈፀም እኮ በፀሎት ከፈጣሪ ጋር ተነጋግሮ መግባባት ይቀላል… ይሄን አውቆ እዛ ተሰቅሎ ከሰው ከፍ ያለ ቦታ ላይ ሲቀመጥ ሰው ዝቅ አድርጎ ይገምታል! እኔ የኛ ሊቀመንበር ይገርሙኛል እንዳለፈበት አራዳ የዝቅተኛነት ስሜት ከተሰማህ ዛፍ ላይ ውጣ አይነት ፕሪንሲፕል ሲጠቀሙ እናደዳለሁ፡፡ ጊዜ ያወጣውን ጊዜ ያወርደዋል እና ጊዜ ያወጣውን እውቀት አስኪያወርደው አስከዛው ልብ ይሰጣቸው ብለን የደንብ የስራ ሂደት ባለቤት እስኪመጡ ልጠብቅ አስቤ ነበር! ነገር ግን የስራ ሂደት ሀላፊው እንደ ሙሽራ ደንበኛ ካላስጠበቁ ቢሮ ድርሽ አይሉም… መንግስታችን መልካም አስተዳደርን አረጋግጣለሁ ብሎ ሌት ተቀን ይቀደዳል እሳቸው መልካም ህዝብ በስልጣናቸው ከስክስ ይረጋግጣሉ!

     በተረገመ ሌላ ቀን ደሞ በከተማ ግብርና ለመደራጀት አንድ ለአምስት በሚባል ጥርነፋ እራሴን ላስር ተገኝቼ ነበር ………ልክስክስ እኮ ነኝ! አዲስ አበባ ላይ ሜካናይዝድ በሆነ የእርሻ መሳርያ ሰሊጥ ፣ ኑግ እና ለውዝ የምናመርት መስሎኝ ወደ ቀበሌ ከማምራቴ በፊት የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲ ጋር በመሄድ ምርት ተቀባዬችን ከሊስታቸው ውስጥ አፈላልጌ ጨርሼ በስልክ ደውዬ ቀብድ ሁላ ሊሰጡኝ ተስማምተው የመንደር ውል ሁላ ተዋውዬ ጨርሼ ነበር …………… ዳሩ ምን ዋጋ አለው እጣ ሲጣል የደረሰን አሳ እርባታ ነበር… ይታያቹ አዲስ አበባ ላይ ታንኳ ቀዝፌ መረብ ዘርግቼ አሳ እያታለልኩ ሳጠምድ! ? ቀበናን ነው አቃቂን ልጠቀም ነው…
ያው እኔ ድሮም ታቃላቹ በጀርባዬ ብወድቅ እንኳን የሚሰበረው አፍንጫዬ ነው።

     በተረገመ ሌላ አንድ ቀን ደግሞ የቀበሌውን ብክነት ሊቀንሱ በሚችሉ ጉዳዬች ላይ ለመወያየት ተገኝቼ ነበር ስልጠናው የሶስት ቀን ቢሆንም በመጀመሪያው ግማሽ ቀን ላይ ሶስት ቀን ማባከን ምንድነው? በሚል ጉዳይ ላይ ለግማሽ ሰአት ተወያይተን ስልጠናው አልቆ የሶስት ቀን አበል ተከፍሎን ከአሰልጣኛችን ጋር ኪስ ሳንገባ የህዝብ ገንዘብ መንትፈን ብክለትን በፍሳሽ መልክ አስወግደን አልፈናል!

     እንግዲ መሬት የመንግስት ነው ይሉናል እኛ ስንማር መንግስት ማለት ህዝብ ነው ተብለናል! ታድያ ለመኖሪያ የሚሆን መሬት ስጡን ድርሻችን ስንል በሊዝ ግዛ ትባላለህ አንድ አባት ትርፍ የነበራቸውን መሬት ይዘው የቆዩ ቢሆንም ይሄን ያህል ብቻ ነው በካርታ የምንሰራሎት የተቀረውን በሊዝ ነው የሚገዙት ሲባሉ! …ሆ! ሊዝ ደሞ የምን ሀገር ገንዘብ ነው ብለው የጠየቁት አንዱ ማሳያ ነው!

     ሌላው ከዚህ ጋር ተያይዞ ትንሽ ጆሯቸው የሚሸውዳቸው አንድ አባት ነበሩ እና ሁሌ በሬዲዬና በቲቪ የእገሌ ቀበሌ ነዋሪዋች ለአባይ ግድብ የሚሆን "ቦንብ" ገዙ፤ የእገሌ ድርጅት ሰራተኞች ከወር ደሞዛቸውን ለአባይ ግድብ የአስር ሚሊዮን ብር "ቦንብ" ገዝተው አጋርነታቸውን ገለፁ የሚል ዜና በዝቶባቸው ነበር፡፡ ሰውየው ለልጃቸው አንድ ጥያቄ አነሱ ህዝቡ ግን ምን ሆኖ ነው ልጄ ለአባይ ለአባይ እያለ ቦንብ የሚገዛው ግብፅ ሳንሰማ ጦርነት ጀመረች እንዴ?… የታሪክ ባላንጣችን እስዋ ነች!… ልጅ ቀበል አደረገና አይደለም አባት ያው ቦንብነቱ ባይካድም ለማለት የፈለጉት ቦንድ ነው፡፡ ቦንድ ደሞ ምንድነው ልጄ?…… ሌላ ጥያቄ? አባ በባንክ የሚሰጥ የመተማመኛ ወረቀት ነው ቦንድ ማለት! …አሀ አባይን ፈርማቹ ለግብፅ ለመስጠት ነው ወረቀት ለአባይ የምትገዙት ግብፅ በባንክ መክፈሉዋ ነዋ ልጄ?…… እረ እንደዛ አደለም አባ! አባይን በህዝብ ገንዘብ መንግስት ገድቦ ለኛ መብራት ያለማቋረጥ እንዲደርሰን ማዋጣት ስላለብን ለተወሰነ ወቅት ወጪ የማይደረግ ገንዘብ ለባንኩ መስጠት ማለት ነው!…… አሀ መብራት እንዳይቋረጥ ነው እንዴ ደግ…መብራትማ ይቋረጥ እንጂ በታወቀ ሰአት ማጥፋት አስለምዶን ሙሉ ቀንማ መብራት  የለበትም… አሁን አህትህ እዛ የኤሌትሪክ አስቶቭ ላይ ሰርታ ከዛ ያጠፉታል አባዬ አታስብ ብላኝ ነው ምትሄደው… እንዲ ያለማቁዋረጥ ከለቀቁልንማ አሳስተው ከነ ድስታችን ያነዱናል… ይሄ መልካምም አገዳደል አደለም !

የኢትዬጵያ ህዝብ እኮ ጨለምተኛ ነው።
ምክንያቱም……
መብራት በአግባቡ አያገኝማ!

እንደ ኢትዬጵያ ደሞ መልካም አስተዳደር ፣ ዲሞክራሲ ፣ ነፃ ነት ፣ የቡድን እና የግለሰብ መብቶች ፣የመናገር፣ የመፃፍ እና ወዘተ መብቶች በእኩልነት የተረጋገጡባት ሀገር የትም የለ

በተገባር እኮ አደለም በከስክስ ነው የተረጋገጡት!

Sunday 13 August 2017

ለምን ጎንደርን? (ሰሜን ጎንደርን ለ 3 ዞን መሰነጣጠቅ ያስፈለገበት ፓለቲካዊ ምስጥር)

(በደርብ ተፈራ)

እርስ በርስ ህዝብን በማጋጨትና አንዱ ከሌላው እንዳይግባባ በተለያየ ፓለቲካዊ ሴራ መከፋፈል የለመደው አገዛዝ ጎንደር ላይ ተጨማሪ ሰይጣናዊ ስራውን ሊፈፅም ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡

ሰሞኑን ሪፓርተር ጋዜጣ እንደዘገበው ሰሜን ጎንደር ለ3 ትንንሽ ዞኖች ሊሰነጣጠቅ ነው፡፡ 16 ወረዳዎችን ያቀፈው ሰ/ጎንደር ዞን ዛሬ ላይ ትልቅ አደጋ ተጋርጦበታል፡፡ ይህ ዞን እንደ CSA (2007) መረጃ ከሆነ  2,929,628 የሚደርስ ህዝብ በስሩ ያቀፈ ነው፡፡ ዞኑ የመሰረተ ልማት እጦት እንዳለበት ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ሲገልፁ እንደነበር ይታወሳል፡፡ የአለም ባንክ በወርሃ ግንቦት 2004 ላይ ባወጣው መረጃ መሰረት በዞኑ የነበረው የኤሌክትሪክ አቅርቦት ከ 7% ነዋሪዎች በስተቀር  ቀሪውን ማዳረስ ያልቻለ ነበር፡፡ ይህን መሰል ችግሮች እያሉ የህዝቡን የልማትና ፍትህ ጥያቄ ችላ ያለ መንግስት ለመከፋፈል ሲሆን ግን ሌት ተቀን ይሰራል፡፡
በከፋፍለህ ግዛ ስልት የተካነው ኢህአዴግ የማንነት ጥያቄ ሲነሳ አማራ ክልልን የሚከፋፍል ከሆነ በደስታ ይቀበላል፡፡ ካልሆነ ግን ጆሮ ዳባ ልበስ ይላል፡፡ ለዚህ ማሳያ ቅማንት ላይ የሰሩትን ማየት በቂ ነው፡፡ የፌደሬሽን ም/ቤት ያመነበት እንኳ አምስት (5) ማህበረሰቦች የማንነት ጥያቄ አቅርበው ጉዳያቸው እልባት አላገኘም፡፡ የቅማንትን ጉዳይ ግን ጎንደርን ለመከፋፈል ስለሚጠቅም አራገቡት፡፡ ተሳካላቸውም የቅማንት ህዝብ የራሱ አስተዳደር ሊሰጠው እንደሆነም ታውቋል፡፡

 የማንነት እና የራስ ገዝ አስተዳደር ጥያቄዎች ሲነሱ በድብቅ ሲያፍን፣ ሲገድ፣ ሲያስር እና የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ሲረግጥ የነበረ መንግስት በራሱ ጉልበት ጎንደርን ለማዳከም በዞን ሲሰነጣጥቅ ማየት ያሳዝናል፡፡ በቁጫ እና ኮንቶማ ማህበረሰቦች ላይ ጥያቄ ባነሱ በምላሹ ምን እንደተደረገ የምናቀው ጉዳይ ነው፡፡

በያዝነው አመት ግንቦት ወር ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በአፋር ክልል አብዓላ ወረዳ የሚኖሩ የትግራይ ብሔር ተወላጆች ያቀረቡትን የልዩ ወረዳ ጥያቄ ውድቅ ማድረጉን ሰምተናል፡፡ ነዋሪዎቹ  “የማንነት መብታችን ቢከበርም ራስን በራስ የማስተዳደር መብታችን ተሸራርፏል” የሚል ቅሬታ ለክልሉ አቅርበው ነበር። ከዚህ በተጨማሪ ተወላጆቹ “ቋንቋችን፣ ባህላችንና ታሪካችንን የምናሳድግበት ሁኔታ አልተመቻቸልንም” በማለት ጥያቄ እንዳቀረቡም ተመልክቷል። የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትም ጉዳዩን አጥንቶ አመልካቾቹ “ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብት የሌላቸው በመሆኑ ያቀረቡትን ጥያቄ ውድቅ አድርጎ ነበር” ተብሏል በወቅቱ በሰማነው ዘገባ፡፡ ይህን ጉደይ ያነሳሁት ምን ያክል ሌሎች ክልሎች ከአማራ ክልል የተሻለ የመወሰን ስልጣን እንዳላቸው ነው፡፡ አማራ ክልል ሲሆን የፌደራል መንግስት ጣልቃ ገብቶ ይፈተፍታል፡፡ እዚህ ላይ የማንነት ጥያቄ የተመለከተ ሀሳብ የተነሳው የመንግስትን ውሳኔ ለመታዘብ እንጅ ከጎንደሩ እውነታ ጋር የተገናኘ ስለሆነ አይደለም፡፡ የጎንደሩ አንድን ህዝብ በዞን ከፋፍሎ ማዳከም ነው፡፡

እስኪ ከዚህ የፓለቲካ ሴራ በስተጀርባ ካሉት አነሳሽ ምክንያቶች መካከል የተወሰኑትን እንይ፦

ሀ. ጎንደር አካባቢ የተነሳው የተቃውሞ ትግል ላይ ቀዝቃዛ ውኃ ለመቸለስ

መንግስት ከወደ ጎንደር ከፍተኛ የሆነ ተቃውሞ እየገጠመው ስለተቸገረ ጎንደርን በመንደር አስተሳሰብ አስሮ ትንሽ ፋታ ለማግኘት ያሰብ ይመስላል፡፡ ሰ/ ጎንደር በዞን መሰነጣጠቁ እርስ በርስ የጥቅም ግጭት እንድነሳ እና የጎንደሬነት ስሜት እንድቀዘቅዝ ማድረጉ አይቀርም፡፡ ይህ ደግሞ ለመንግስት በለስ የቀናው ያክል ነው፡፡

ለ. አማራን በተለያየ ዘዴ ለማዳከም

ገለን ቀብረነዋል ያሉት አማራ መቃብር ፈንቅሎ የወጣ ስለመሰላቸው በቻሉት መጠን ከፋፍለው እየቅል መምታት ይፈልጋሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ የጎንደሩ አይነት ሴራ ተቀዳሚ አማራጭ ነው፡፡ ቢቻላቸው አማራ የሚባል ህዝብ ከምድረ ገጥ ቢጠፋ ይደሰታሉ፡፡ ይህ ባይሳካ ደግሞ እርስ በርሱ ማናከሱ ቀሪ አማራጭ ነው፡፡ ገና ብዙ ነገር እናያለን፡፡ ተንኮላቸው ገደብ የለውም፡፡

ሐ. በመልካም አስተዳደር ስበብ ህዝብን ማታለል

ሰ/ጎንደር ብዙ ህዝብ የሚኖርበት ዞን ስለሆነ ለአገልግሎት አሰጣጥ አይመችም የሚል ስንኩል ምክንያት እያቀረቡ እንደሆነ በሰማን ጊዜ ተገርመናል፡፡ ይህ ከሆነ ለምን ደቡብ ክልል የሚነሱ መሰል ጥያቄዎችን አይመልሱም፡፡ ለምን ጎንደርን? የመልካም አስተዳደሩ ችግር ለጎንደር ህዝብ ያላቸው ጥላቻ መገለጫ እንጅ የህዝብ ብዛቱ ያመጣው አይደለም፡፡ ወረዳዎች የተዋቀሩት ለተመሳሳይ አላማ አልነበረምዴ? በዞን መሰነጣጠቁ ምን የተለየ መፍትሄ ይዞ ሊመጣ? በመልካም አስተዳደር ሰበብ የሚደረገው ሴራ ተቀባይነት የለውም፡፡

ጎንደር ላይ የታቀደው ሴራ በክልሉ ም/ቤት ከፀደቀ ጎንደር አደጋ ላይ ወደቀች፡፡ በዞን የመሰነጣጠቁ ሀሳብ በክልሉ ካቢኔዎች ሙሉ ድጋፍ ያገኘ እንደሆነ ሪፓርተር መዘገቡ ይታወሳል፡፡ አሁን የቀረው የክልል ም/ቤት ውሳኔ ብቻ ነው፡፡ መንግስት ያላወቀው ነገር  ጎንደር በዚህ እና መሰል ተንኮል ተስፋ እንደማይቆርጥ ነው፡፡


Thursday 3 August 2017

ዕውቀትን በጋሻ የሚከላከል ትውልድ

By Derbe Tefera


ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በታችኛው የትምህርት እርከንና በዩኒቨርሲቲዎቻችን አካባቢ የዕውቀት ድርቅ እየተከሰተ እንደሆነ ብዙዎች ይገምታሉ፡፡ በሃገራችን የትምህርት ታሪክ የንባብ ወኔና ፍቅር የነበራቸው ተማሪዎች ከንጉሱ ስርዓት ጋር ዳግም ላይመለሱ የጠፋ ይመስላል፡፡በ1960 እና 70ዎቹ የነበረው የተማረ ትዉልድ ከሚታወቅባቸዉ ነገሮች መካከል ለሃገር እድገት ፣ አንድነት ፣ ለፍትህ ፣እኩልነት ፣ ነፃነት መታገል እንድሁም ጠንካራ የንባብ ባህል እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡ አሁን ላይ ግን በተቃራኒው በትምህርት ተቋማት አካባቢ መሃይምነት ሞቅ ያለ አቀባበል እየተደረገለት ነው፡፡ተማሪዎች ለትምህርት ያላቸው ቦታ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ኩረጃን እንደ ዘመናዊነት በመቁጠር አውቆ ማግኘት የሚለውን ብሂል እያጠፋን ነው፡፡ፈተና ይኮረጃል ፣ ለምረቃ የምርምር ስራ ይቀዳል ፣ የቀለም አባትና ልጅ እርስ በርስ መከባበር ቀርቷል፤ በትምህርት ዓለም ኩረጃ የለመደ ትውልድ በስራ ዘመኑ፥
❖የህዝብን ካዝና ላለመዝረፋ ፣
❖ፍትህ ላለማዛባቱ ፣
❖የመልካም አስተዳደር እንቅፋት ላለመሆኑ ፣
❖የሃገር ሸክም ፣
❖ግብረ-ገብነት የጎደለው ፣
❖የማህበረሰቡን ሰላም አደፍራሽ ፣
❖የነፃነት ካቴና ላለመሆኑ እና የችግሮች ሁሉ ምንጭ ላለመሆኑ ምን ዋስትና አለን፡፡

በመጨረሻም ሰራው አጋልጦት "ዳኛና ወራጅ ውሃ ከፊት ያገኘውን አይለቅም "እንደሚባለው ተይዞ ከታሰረና ለዓመታት ከተቀጣ ወጣት ሆኖ ገብቶ ከማረሚያ ቤት ሸበቶ አብቅሎ ይወጣና ከዘራ ይዞ በፀፀት ጎዳና ቀሪ ህይወቱን ይመራል፡፡የሚያሳዝነው ነገር ለራሱ ፣ ለቤተሰብ ፣ ለአደገበትና ላሳደገው ማህበረሰብ እንድሁም ለሃገር ምንም ሳይጠቅም የሞራል ልዕልናም ሳይኖረው ፤
የትም ውሎ ከቤት ፣
ኑሮ ኑሮ ከሞት
መቅረት አይቻልም እንደሚባለው እለተ ሞቱ መድረሱ ነው፡፡

ልክ ጥሬ ዕቃ እንደሌለው ፋብሪካ፥ ጭንቅላቱ የዕውቀት እርሾ የሌለው ባዶ (ለማለት ቢከብድም) ትውልድ መፈጠሩ አይቀርም እየተፈጠረም ነው፡፡/ጥቂቶችን አይመለከትም፡፡ ጅምላ ፈፍረጃ አይደለም፡፡/
ችግሩ ከምንም በላይ ያስፈራል፡፡ ለነገሩ ፦

✿አጥንት የሚወጉ የጤና ባለሙያዎች + ከልምድ አዋላጆች የማይሻሉ ፣
✿ስማቸውን መፃፍ የሚከብዳቸው ምሩቃን (የተጋነነ አይምሰላችሁ ያጋጠመኝ ነገር ነው
✿የሳይኮሎጅ ምሩቅ ሆነው ለማህበረሰቡ የምክር አገልግሎት መስጠት ሲገባቸው ራሳቸውን ከስነ-ልቦና ቀውስ ማውጣት ያልቻሉ፣
✿ ፍ/ቤቶች በደመነፍስና በልምድ ከህግ ዕውቀት ነፃ በሆነ ትውልድ ሲጥለቀለቁ ማየት ያላሰፈራ ከቶ ሌላ ምን ያሰፈራል፡፡

በብዙዎቻችን ዘንድ መማር ከኃላ ቀርነት ፣ ከድህነት እና ከድንቁርት መላቀቅ ሳይሆን መማረር ሲያልፍም በተቃራኒው እየታየ መጥቷል፡፡
አልፈልግም ድግሪ ፣
ይቅርብኝ ማስትሬት ፣
ስንዝሯ ይበቃል ፣

የሰበታ መሬት፡፡ እንደተባለው ወገኖቻችን ከዕውቀት ማዕድ ላይ ተነስተው በቢዝነስ ጎዳና ላይ መጓዝን ምርጫቸው እያደረጉ ነው፡፡ ሃገር በዕዉቀት ድርቅ ለመመታቷ ሌላ ምን ማረጋገጫ ይኖራል፡፡ በስራ ላይ ያለዉ የተማረዉ ሃይል ስራውን እየተወ መውጣት ከጀመረ እና ልመምድ በሌላቸው ከመንግስት የስራ ባቡር ለይ ተሳፍረው ቅርብ ወራጅ በሆኑት መተካት ከተጀመረ ቆየ፡፡ይህ ጉዳይ ከደመወዝ እና ሌሎች ጥቅማጥቅሞች ጋር በቀጥታ ይገናኛል፡፡ ሰለዚህ መንግሰት የራሱን አሳይመንት ሊወጣ ግድ ይለዋል፡፡ በፊት የነበረው የተማረ ሰው ክብር ዛሬ ላይ የት ደረሰ?

በመማርህ ሁለት ጊዜ አትሰደብ፡፡ይህን ያልኩት ወድጀ አይደለም፥ አንድ ሰው እንድህ ሲል አጫወተኝ ፦ ስድብ እንኳን ተቀይሮ በፊት አንተ የምን ልጅ ይባል የነበረው አሁን አንተ የመንግስት ሰራተኛ እና አንተ የመምህር ልጅ በሚል ሊቀየር ነው ብሎ ቀለደ፡፡

ወገኖቸ አንተ የተማርክ መሐይም ከሚለው የሁለተኛው ስድብ ይሰውረን እላለሁ፡፡ዛረሬ ለላይ በመማርህ ትሰደባለህ ፣ ተምረህ ባለማወቅህ ግን የበለጠ ትሸማቀቃለህና ከንባብ አትመለስ፡፡ "The one who graduated yesterday & stop reading today is uneducated tomorrow" ይባላልና ትምህርት ማለቂያ ሰለሌለው እንድሁም የምታውቀውን ነገር "update" ማድረግ ሰላለብህ የመንግስት ሰራተኛ ከሆንክ ዋናውን እንጀራ ማግኘት ቢከብድህም ከ አ/አ ሰጋቱራ እንጀራ መስል የእንጀራ "High Copy" ራስህን እየጠበክ አንብብ፡፡ ሰጋቱራ ግን ሌላ ድርቀት ነውና ተከላከለው፡፡ የሆድ እና የዕውቀት ድርቀት ከያዘህ አገርህን መጥቀም አትቸችልም፡፡
እውቀትን ሳይሆን መሃይምነትን በጋሻ አእንከላከል፡፡ የቢዝነሱ ዓለምም ዕውቀትን ይፈልጋልና ሱቅ በደረቴ ሆነህም እንዳትቀር ዕውቀት ሊኖርህ ይገባል፡፡

ዘላቂዉ መፍትሄ ምን ይመስላችኃል??????

የሃሰት ምስክርነትና መዘዞቹ


By Derbe Tefera

በሃገራችን ለዘመናት የፍትህ ስርዓቱን ሲፈታተኑት ከቆዩትና ዛሬም ማስወገድ ካልቻልናቸው ጉዳዮች/ተግዳሮቶች መካከል አንዱ ነው ***የሐሰት ምስክርነት***፤ይባስ ብሎ ከጊዜ ወደ ጊዜ በማህበረሰባችን ዘንድ እንደ ነውር መቆጠሩንም እየረሳን መጥተናል፡፡ ዓለም ለእምነታችን ባለን ጥንካሬ ማረጋገጫ የሰጠችን እና ሰለ እውነት ይሞታሉ የምንባል ህዝቦች እነሆ ዛሬ ላይ እሴቶቻችን እየጠፉ ስለ እውነት መኖርን በመተው በሐሰት ጎዳና መኳተን ከጀመርን ሰነበትን፡፡

በሐሰት ምሰክርነት መዘዝ የተነሳ ምንም ሳያጠፉ ፀጉራቸውን ተላጭተው ከርቸሌ የወረዱትንና ወንጀል ሰርተው ግን ነፃ ናችሁ ተብለው የሰላም አየር የሚተነፍሱትን ዜጎች ቁጥር እኛ ሰለማንደርስባቸው አሳይመንቱን ለፈጣሪ ሰጥተናል/ፍትህ ሚ/ር እንኳን አይችለውም/
ህሊናችን ካልገዛን በስተቀር ፍ/ቤቶች ምንም ያክል ጠንካራ ስርዓት ቢዘረጉ ችግሩን ማስቀረት አይችሉም፡፡
በፍትሃ ብሔር ስነ-ስርዓት ህግ ቁ 263 ላይ እንደተደነገገው ለምስክሮች አራት /4/ አይነት ጥያቄዎች ይቀርባሉ፡፡ እነዚህም ፦
1ኛ. ዋና ጥያቄ /Main examination/
2ኛ.መስቀለኛ ጥያቄ/ Cross examination/
3ኛ.ማጣሪያ ጥያቄ/Re-examination/
4ኛ.መሪ ጥያቄ/Leading question/ ናቸው፡፡ ምስክር ቃሉን ከመስጠቱ በፊት መሃላ ይፈፅማል አልያም የሚሰጠው ቃል እውነት መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ መፍትሄ ግን ሲሆን አላየንም፡፡ አሰራር ሰለሆነም ተቃውሞ የለንም፡፡


ህጉ ይህን ቢልም በተግባር ግን በዝምድና ፣ የተለየ ጥቅም በመፈለግ ፣ በሃይል ጫና በመፍጠርና በሌሎች ምክንያቶች ሰው ህሊናውን እና ፈጣሪውን ክዶ በሐሰት ይምላል ፤ ይመሰክራል፡፡
የድርጊቱ ጉዳትም የትየለሌ ነው፡፡ "የአይጥ ምስክሯ ድንቢጥ" እንደሚባለው ሆነና ነገሩ ፍትህ ላይመለስ ከሃገራችን ሰማይ ራቀ፡፡ ፈጣሪም መታዘቡንና በኛ ማዘኑን ቀጠለ፡፡ እስከመቼ???
ለነገሩ ****Justice is sold at a high price*** ይሉ የለ ፈረንጆችስ፡፡
ኧረ ፍትህ እንደ ውሃ ጠማን ፥ ማነው ተጠያቂ? መንግስት? ህዝብ? ወይስ ሌላ አካል?
ለፍትህ ስርዓቱ በዕንቅርት ላይ ጆሮ ገድፍ የሆነው ፨የሐሰት ምስክርነት ፨በእስካሁኑ ይብቃ፡፡
ለህሊናችን እንገዛ!!!


በሌሎች የዳኝነት ችግሮች ላይ እመለሳለሁ፡፡

ትምህርትን እንደ ትውልድ ማደንዘዣ

(በደርብ ተፈራ)

ይሄ ትውልድ የማወቅ ፍላጎቱን የተቀማ ነው፡፡ የተማረ ሰው ክብር ሲያጣ መማር በራሱ ይረክሳል፡፡ በታዳጊ አገሮች ትምህርት እንጀራ ነው፡፡ በእነዚህ አገራት ለማወቅ ብቻ የሚማሩ ካሉ እነሱ ብፁዓን ናቸው፡፡ ቢቻል የሰው ልጅ ለአዕምሮው ምግብ የሆነውን እውቀት በሆዱ ባይቀይረው መልካም ነበር ባይሰበር፡፡ መቼ ይሆን ግን ከድህነት ተላቀን ለማወቅ የምንማር?

‹‹ተማር ልጄ ወገን ዘመድ ሀብት የለኝም ከጄ፤
ላልተማረ ሰው ቀኑ ጨለማ ነው፡፡››

     ‹‹ያልፍልኛል ብለህ ወጣትነትህን በትምህርት ዓለም ካሳለፍክ በኋላ ማለፉ ቀርቶ ጊዜው ሲያልፍብህ ምን ይሰማሀል?›› ያኔ ነው ላልተማረ ሰው ቀኑ ጨለማ ነው የሚለው የዘፈን እንጉርጉሮ ለተማረ ሰው ቀኑ ጨለማ ነው ተብሎ መቀየር ያለበት፡፡ በድሮ ጊዜ ‹‹ትምህርት መራራ ናት ፍሬዋ ግን ጣፋጭ ናት›› ይባል ነበር አሉ፡፡ አሁን አሁን ግን ተምረህ የድህነት ሰርቲፊኬት ይዘህ ቤትህ ትመለሳለህ፡፡ ትምህርትና ፍሬዋም እንደ ሬት ይመሩሀል፡፡ መተኪያ የሌለውን እድሜህን ለትምህርት ሰውተህ በስተመጨረሻ ሜዳ ላይ ስትወድቅና የእውቀት ኢንቨስትመንት ቦታ ስታጣ ምን ትላለህ? ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ እንደሚባለው ተመርቆ ስራ ማግኘት ቀላል የሚመስላቸው ጥቂቶች ብቻ  አይደሉም፡፡ ነገሩ ግን እጅጉን ከባድ ነው፡፡ በጣም ያስጨንቃል፡፡ ረፍትም ይነሳሀል፡፡  ከራስህ ጋር ጦርነት ውስጥ ትገባለህ፡፡


     እድለኛ ከሆንክና ዘመድ ካለህ ወደ አንዱ የመንግስት መስሪያ ቤት ወይም የልማት ድርጅት ሸጐጥ ትላለህ፡፡ ይህ ካልተሳካልህም  ወደ ግል ድርጅቶች ሰፈር ሁነኛ ሰው ካለህ ምንም አይጨንቅህም፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውስጥ ‹‹ዘመድ እንጅ ልምድ›› አይደለም የሚፈለገው፡፡ በብርሃን ፍጥነት ደምወዝተኛ ትሆናለህ፡፡ ዘመድ ሳይኖርህ እውቀትና ልምድ ቢኖርህ የትም አትደርስም፡፡ አልፎ አልፎ ሁሉንም ሰንሰለት መበጣጠስ የሚችሉ ብቃት ያላቸውን ሰዎች ግን አይጨምርም፡፡ የተወሰኑ መስሪያ ቤቶችም በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ አይካተቱም፡፡


     በዘመዶችህ ትግልና ውለታ መንግስት ቤት ከገባህና ብልጥ ሆነህ ሲጠሩህ አቤት ሲያዝዙህም ወዴት ካልክ ወድያውኑ ስልጣን ይሰጥሀል፡፡ በልማታዊ ዘፈን መጨፈር ትጀምራለህ፡፡ በአብዮታዊ ድሞክራሲም ፈርሰህ እንደገና ትገነባለህ፡፡ እኛ ስለማናውቃት ኢትዮጵያም ማውራትን ትለማመዳለህ፤ የፓርቲ ታማኝነትህና የፖለቲካ ቁርጠኝነትህ እየታየ በሂስ ግለ ሂስ መከራህን አይተህ ሂስህን በልማታዊ ድስኩር አወራርደህ እና በአብዮታዊ ድሞክራሲ ውጠህ አቋምህ ይታይና ታዛዥ ከሆንክ ከጥቃቅንና አነስተኛ የስልጣን ቦታህ ወደ መካከለኛው እርከን ቀስ እያለም ወደ ከፍተኛው የአመራር ደረጃ የሚያበቃህን ስንቅ ትይዛለህ፡፡ ምንም አይጭነቅህ ታዛዥ ስብዕና ካለህ በእኛ የፖለቲካ አሰራር ቢችሉ ጨረቃ ላይም ይልኩሀል፡፡


     በተለይ ደግሞ እነሱ የሚሉህን የምትል ከሆነ አንተ የቁርጥ ቀን ልጅ ነህና ቁርጥ እየበላህ ስለ ደቡብ ኮሪያ፣ ታይዋንና ሲንጋፖር የልማታዊ መንግስትነት ተሞክሮና ያንተ አገር ስለምትከተለው መንገድ ትክክለኛነት ምስኪን ዜጎችን ሳይወዱ በግዳቸው አዕምሯቸውን እየደፈርክ ፕሮፓጋንዳህንም እየጋትክ ፅድት ባለ መኪና ትንፈላሰሳለህ፣ በብዙ ካሬ ሜትር ላይ የተንጣለለ ቪላ ቤትም ይኖርሀል፡፡ አለም ተራ ነውና አንተም እንደ ዘመዶችህ የምትወዳቸው ቤተሰቦችና ዘመድ አዝማድ ሁሉ ከሥራ አጥነት ትታደጋለህ፡፡ ምድራዊ ገነትም ትፈጥርላቸዋለህ፡፡ አለፍ ሲልም ለጓደኞችህ ጓደኞች ሳይቀር መከታ ትሆናለህ፡፡ ግን ግን አንተ ደናቁርት ስለሆንክ አስተሳሰብህም በዛው ልክ የወረደ መሆኑን አትዘንጋ፤ ለተማረ መሀይም ጥሩ ምሳሌም ነህ፡፡ ከእውቀት ማነስ የተነሳም አስተሳሰብህ ሻግቷል፡፡


     የሰፊው ህዝብ ልጆች ጥራት በሌለው የት/ት ስርዓት እየመከኑ አንተ ልጆችህን ከፈለክ አውሮፓ ደስ ካላለህም አሜሪካ ልከህ በእውቀት ተኮትኩተው ያድጉልሀል፡፡ አይበለውና አንድ ቀን የምትመካበት ስርዓት ራሱን በራሱ ቢያጠፋ ወይንም ህዝባዊ እምቢተኝነት እና ቁጣ ገርስሶ ቢጥለው ሳትውል ሳታድር በጨረቃ አገሪቱን ለቀህ ወደ ውጭ ትፈረጥጣለህ፡፡ በባዕድ መሬትም አገር አማን በሆነበት ወቅት በዘረፍከው ገንዘብ ተንፈላሰህ የድሎት ኑሮ ትኖራለህ፡፡ የሰው ልጅ በጭንቅላቱ እንጅ በሆዱ አያስብም፡፡ ለሆድህ ኖረሀልና ከህሊና ፍርድ አታመልጥም፡፡ አንድ ቀን በስራህና በሰራኸው ስራ ትፀፀታለህ፡፡ የሰው አገር የሰው ነውና ዞረህ ዞረህ አገርህ ስለምትናፍቅህ ወደ እናት ኢትዮጵያ ለመምጣት ማሰብህም አይቀርም፡፡ ጭንቅላት ሆድ የሆነበት ህይወትህ ተቀይሮ ነፍስህ በጥያቄ እረፍት ታሳጣሀለች፡፡ የትውልድ ክፍተትም ፈጥረሀልና መጥፎ ውለታህ መቼም አይረሳልህም፡፡ አንተን ተከትለውም እልፍ አዕላፍ ወገኖች በተሳሳተ የህይወት መንገድ ተጉዘዋል፡፡


     ይህ ሁሉ የሚያመላክተው በትምህርት ዓለም ውስጥ እያለህ ግብህን ሳትመታ መቅረትህን ነው፡፡ የትምህርት ውጤት እውቀት፣ ክህሎትና መልካም ስነ ምግባር ናቸው ካልን አንተ ከእውቀት ነፃ፣ ክህሎትም ችሎታም የሌለህ ምግባረ ብልሹ ሰው ነህና የዘራኸውን ማጨድህ አይቀርም፤ መቼም አንድ ገበሬ ማሳው ላይ ጤፍ ዘርቶ እያለ መኸር ሲደርስ ከማሳው ስንዴ አያጭድም፡፡ እትብትህ የተቀበረባት አገርህና ከእለት ቁርሱና ጉርሱ ቀንሶ ያስተማረህ ህዝብም የህሊናህን ጥያቄ በቀላሉ እንዳትመልስ ያወሳስብብሀል፡፡ ከአገርህ ብሄራዊ ጥቅም አስበልጠህ ለግላዊ ጥቅምና ፍላጎትህ ባሪያ ሆነዋልና አንተ ለማንም አትጠቅምም፡፡ መሪ ማለት እኮ ትክክለኛውን መንገድ የሚያውቅ፣ መንገዱን ለሌሎች የሚያሳይ ብሎም በመንገዱ የሚሄድ ማለት ነው፡፡ አንተ ግን ትክክለኛውን መንገድ ሳታውቅ ሌሎችንም በስህተት ጎዳና አስገብተህ በተሳሳተው መንገድ ስትጓዝ ኖርክ፡፡ ይብላኝልህ! እርጅናውም መጣ ሞቱም አይቀርልህ፡፡ ባትወለድ ይሻል ነበር ከንቱ ሆነህ ተወልደህ ከንቱ ሆነህ ኖረህ በከንቱ አለፍክ፡፡ ያንተ መጨረሻ እንድግድህ ይሄ ነው፡፡


     ካምፓስ ላይ ቀልዳችሁ በስራው አለም ደግሞ የሚያግዛችሁ ዘመድ ከሌላችሁ ከሁለት የወጣ ጎመን ማለት ከናንተ ሌላ የለም፡፡ አንደኛ ከእውቀቱ ባህር አልጨለፋችሁም፡፡ ሁለተኛ በባሌም በቦሌም ብላችሁ ስራ ቢጤ አልያዛችሁም!፡፡ በዚህ የተነሳ ‹‹ሜዳ ላይ ቀረሁኝ›› አይነት ዜማ ድንገት በአዕምሯችሁ እየመጣ ይረብሻችኋል፡፡
     ሰለ ምረቃ ለማውሳት ያክል እንዳይደርስ የለምና የተማረ ሰው የነበረውንና ዛሬ ላይ የተነጠቀውን ቦታና ክብር አስታውሰህ ‹‹ከልኩ ላያልፍ›› በሚል የብስጭት ስሜት ምንም የህይወት ስንቅ ሳትይዝ የካምፓስ ቆይታህ ወደ መጠናቀቁ ተቃርቦ እውቀትን ሳትሸምት ጓደኞችህ ለምረቃ መፅሄት የሚሆን ጥቅስ (ላስት ወርድ) አፈላልግ ልንመረቅ ምናምን ቀን ቀረን ይሉሀል፡፡ ‹‹ሳይጨርሰኝ ጨረስኩት›› (‹‹ላልቅ ስል አለቀ››)፣ ‹‹መመረቅስ በፈጣሪ ነው››፣ ‹‹ምቀኛ ገና ምን አይተሸ››፣ ‹‹ይሄ ሁሉ ጣጣ ለአንድ ባርኔጣ…›› ወዘተ ከሚሉት ጥቅሶች አንዱን መርጠህ ሱፍህን ገጭ አድርገህ፤ ይህም አልበቃህ ብሎ የህዝብ አደራ መሸከምህን አመላካች የሆነውን ጥቁር ጋዋን አጥልቀህ የተነሳኸውን ፎቶ አንዱን ከጥቅሱ ጋር ለምረቃ መፅሄት ሌላውን ለቤተሰብ ብትልክላቸውና ግድግዳ ላይ ቢሰቅሉት ስትሞት ማልቀሻ ካልሆነ በስተቀር ሌላ ፋይዳ አይኖረውም፡፡


      ከትምህርት ተቋማት ሳንወጣ እስኪ ዩኒቨርስቲዎቻችንን ትንሽ እንማቸው፡፡  ዩኒቨርሲቲዎቻችን የመንደር ተቋማት ሆነዋል፡፡ ዩኒቨርስቲ ማለት ዩኒቨርስ ከሚለው ቃል ጋር የተያያዘ ስያሜ አለው ካልን አለም አቀር አድማስ ሊኖረው የሚገባ ተቋም ነው ብለን መውሰድ እንችላለን፡፡ ስለዚህ አደረጃጀቱና እንደ መማር ማስተማር፣ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት የመሳሰሉ ተልዕኮዎቹ አለም አቀፍ ይዘት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ የሰው ሀይል ስብስባቸውም በጎሳ ተዋፅኦ ሊሆን አይገባም፡፡


     ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ የምናገኘው እውነታ ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፕሬዚዳንቶች እና የቦርድ አባላት እንድሁም ዝቅተኛ የአስተዳደር ባለሙያዎች የአካባቢ ተወላጅ ተብየዎች ጥርቅም እየሆነ ነው፡፡ ሁሉም ዩኒቨርስቲዎች ባይባልም አብዛኞቹ የዚህ ችግር ሰለባ ናቸው፡፡ እንደ ማስተባበያ የሚቀርበውም ከተቆርቋሪነት ጋር የተያያዘ ምክንያት ነው፡፡
‹‹እኔ ከሰሜን ከመጣሁ ደቡብ ላይ ላለ ዩኒቨርስቲ ተቆርቋሪም ቆርቋሪም የማልሆንበት
ምክንያት ግን እስከዛሬ አልገባህ ብሎኛል፡፡››
      ይህ የመንደር አስተሳሰብና ጎጠኝነት ጉዳት አለው፡፡ ፀረ-ኢትዮጵያዊነት አካሄድም ነው፡፡ በተቋማቱ ውስጥ ብዝሃነት ሲኖር የተለያየ አመለካከት ይፈጠራል፡፡ ይህ የአመለካከት ልዩነት ነገሮችን ከብዙ አቅጣጫ እንድንረዳ ሲያግዘን የሃሳብ ፍጭቱ ደግሞ ለችግሮች የተሻለ መፍትሄ ለመሻት ይረዳል፡፡ አንድ ሰው ዩኒቨርስቲው ካለበት አካባቢ ስለተወለደ ሳይሆን ብቃቱ ታይቶ ነው አመራር ቦታ ላይ መቀመጥ ያለበት፡፡ የኦሮሞ ምሁር አማራ ዩኒቨርስቲዎች ላይ ባይተዋር ከሆነ የአማራ ምሁር ኦሮሞና ትግራይ ዩኒቨርስቲዎች ላይ ከተገፋ፣  የትግሬ ምሁር አማራና ኦሮሞ ዩኒቨርስቲዎች ላይ ቦታ የለህም ከተባለ፣ ደቡቡ ወደ ክልልህ ዩኒቨርስቲዎች ሂድ ከተባለ…ዩኒቨርስቲዎች አለም አቀፍ ተቋም መሆናቸው ቀርቶ በፌደራል መንግስት ስር መቋቋማቸውም ጥያቄ ያስነሳል፡፡ እውነት እላችኋለሁ ዩኒቨርስቲዎቻችን ላይ ትልቅ አደጋ ተጋርጧል፡፡ የመንደር ፖለቲካ የዬኒቨርስቲዎችን አጥር ጥሶ መግባቱን ስታውቁ እጅጉን ታዝናላችሁ፡፡


     በዩኒቨርስቲዎቻችን አካባቢ እየተፈጠረ ያለው ተመሳሳይ የሆነ የሰው ሃይል ስብስብ ከምክንያት ይልቅ ‹‹በእኔነትና በእነሱነት›› መመዘኛ ተቋሞች እንድመሩ ብሎም የባይተዋርነት ስሜት እንድነግስ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ መልካም አስተዳደር፣ ብልሹ አሰራርና ስርዓት አልበኝነትም በተቋማቱ ውስጥ ይነግሳሉ፡፡ ግልፅነት የተሞላበት አሰራር ይዳከማል፡፡ ውሳኔዎችም ሲተላለፉ ከህግና መመሪያ ይልቅ በግለሰቦች ፍላጎት ላይ ተመስርቶ እንድሆን አስቻይ ሁኔታዎች ይመቻቻሉ፡፡ ተቋማትም አለምአቀፋዊነት  ሳይሆን ሰፈርተኝነት መገለጫቸው  ይሆናል፡፡  በሌላ መልኩ ደግሞ በዩኒቨርስቲዎቻችን አካባቢ እንድሁም ታችኛውን የት/ት እርከን ጨምሮ የብዛት ወይም ተደራሽነት ችግሩ ላይ በማተኮር የጥራቱ ነገር ችላ የተባለ ይመስለኛል፡፡ ጥራት እንጅ ብዛት ለአገር አይጠቅምም፡፡ የቱ ይቅደም የሚለው ግን አድስ ተሰርቶ ያለቀ ቤት ዕቃ እስከሚሟላ ተዘግቶ ይቀመጥ ወይስ እንግባበትና ቀስ በቀስ እቃውን እናሟላ እንደማለት ነው፡፡ ምርጫውን ለእናንተ ትቻለሁ፡፡ በበኩሌ የያዝኩት አቋም ዩኒቨርስቲዎች አይስፋፉ፤ቁጥራቸው አይጨምር ማለት እንዳልሆነ ያዙልኝ፡፡ ግን ምርጫ በደረሰ ቁጥር የመሰረት ድንጋይ እየጣሉ ዩኒቨርስቲ ይገነባልሀል ማለት ቀበሌዎቻችንን ሳይቀር የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ባለቤት ለማድረግ ያሰቡ አስመሰለባቸው፡፡ እንደ አሸን የፈሉ ተቋማት ቢኖሩን አይከፋኝም፤ እኔን የሚያሳስበኝ የሰው ሀይልና የማቴሪያል አቅርቦት ሳይኖር ህንፃ ብቻ ቆሞ ሲቀር ስለታዘብኩ ነው፡፡ ከጥቂት አመታት በኋላ በነርስ የሚማሩ ዶክተሮች እና በድግሪ የሚማሩ ማስተርሶች ሊያጋጥሙን ቢችሉ ውርድ ከራሴ፡፡ ሳንማር እያስተማርን እስከመቼ? ተምረንም የተሻለ ተስፋ ሊኖረን አልቻለም፣ ስለዚህ ማንን እያየን እንማር?


     ‹‹አምሳ ቢወለድ አምሳ ነው ጉዱ ከተባረከ ይበቃል አንዱ›› በማለት በጣት የሚቆጠሩ ዜጎችን አስተምረን ኢትዮጵያን ለእነሱ ብቻ አደራ ሰጥተን ሌሎቻችን እጅና እግራችንን አጣጥፈን ብንቀመጥ ሽክማቸው እጅጉን የከበደ ነው የሚሆነው፤ አመንም አላመንም! ወደድንም ጠላንም አገር በተወሰኑ ግለሰቦች እና ቡድኖች ጥረት ብቻ ልትለማ አትችልም፡፡ ጥቂቶች የተለየ የመሪነት ችሎታ ካላቸው እስኪ ቀስቅሱልኝ ምሁሩ ይነሳ፤ ይከተል የለም ወይ ሌላው በዳበሳ እንደሚባለው ብዙሃኑ እነሱን እያየ ይከተል ይሆናል፡፡ ነገር ግን እነሱ የድህነት፣ ኋላ ቀርነት፣ አምባገነንነት፣ ኢ-ፍትሃዊነት እና ሌሎች የማህበረሰብ እድገት ማነቆዎችን ለመስበር ሲሞክሩ ሰፊው ህዝብ በእውቀትና ክህሎት ካላገዛቸው ልፋታቸው ፍሬ ሊያፈራ አይችልም፡፡ ስለዚህ የሰው አዕምሮ ላይ በሰፊው ኢንቨስት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ባይሆን ግን የሁላችንም ጐጆና መጠጊያ የሆነችው ኢትዮጵያ መፍረሷ እውነት ይሆናል፡፡ የዘመመችዋን ጐጆ ሊያቀናም ሊያፈርስም የሚችለው ህዝብ ነው፡፡ አጥፊዎችም በተናጠል ጐጆዋን ሲነቀንቁ ዝም ከተባሉ ያፈርሷታል፡፡


     ዩኒቨርሲቲዎችም ሲገነቡ ብቃት ያለው የሰው ሃይል፣ በቂ የመፅሃፍት አቅርቦት፣ደረጃውን የጠበቀ የቤተ-ሙከራ አደረጃጀትና ምቹ አካባቢያዊ ሁኔታ እና የመሳሰሉት ከግምት ውስጥ መግባት ይኖርባቸዋል እላለሁ፡፡ የአካዳሚክ ነፃነትም ሊታሰብበት ግድ ይላል፡፡ ይህ ካልሆነ የዘመመችው ጐጆ እንድትፈርስ መሰሶውን በመጋዝ መቁረጥ ነው፡፡
      ወደ መጀመሪያው ሀሳብ ስመልሳችሁ….በአድስ መንፈስና ወኔ ብሎም ለየት ባለ የስራ ፍቅር የትምህርት አመቱን አሀዱ ብየ ጀመርኩ፡፡ ስራውን በይፋ ጀምሬ ቆየትየት ስል ግን ያ ሁሉ ወኔና የስራ ፍቅር ድራሻባቱ ጠፋ፡፡ ለዚህ ምክንያት የሆነው ደግሞ ከተማሪዎች የትምህርት ፍላጎት ጋር የተያያዘ ችግር ነበር፡፡ ከእለታት አንድ ቀን ተማሪዎችን ምን ሆናችሁ ነው የማታነቡት ስላቸው! አንዱ ተማሪ ያው እኛኮ ጊዜ ለማሳለፍ እና ቤተሰቦቻችን ደስ እንድላቸው እንጅ ተምረን ያልፍልናል ብለን አይደለም የምንማረው ሲል  ተናገረ፡፡ በወቅቱ የተሰማኝን ስሜት መግለፅ ይከብደኛል፡፡ ለካ ድንጋይ ላይ ውሀ እያፈሰስኩ ነበር፡፡


     ለነገሩ ተማሪዎቹ ምን ያድርጉ? ፕሮፌሰር ሆኖ ኪራይ ቤት ሲኖር፣ ለማንበብ ሲነሳ ሰዓት አልፏል ብለው የመብራት ቆጣሪ ሲያጠፉበት እና ማንበብ እየፈለገ 500 ብር የሚሸጥ መፅሀፍ እንኳን መግዛት ሲያቅተው፤ ይህ ብቻ አይደለም አቅም ስለሌለው ‹‹በሰማይ ነው ቤቴ›› ብሎ ራሱን እያታለለ ቤት አልባ ምድራዊ ህይወት ሲኖር…ወዘተ እያዩ ተማሪዎች እንደት ይማሩ? ሳይማሩ እያስተማሩ ያሉ የኔ ቢጤ አስተማሪዎችም ራሳቸውን በእውቀት ይገነቡ ዘንድ ከመሰረታዊ ፍላጎት እስር ቤት መውጣት አለባቸው፡፡ እውነት ለመናገር ስለ ዕለት ጉርስህ እያሰብክ የተሻለ የአካዳሚክ ህይወት ሊኖርህ ፈፅሞ አይችልም፡፡ ‹‹ማን ያውጋ የነበረ፣ ማን ያርዳ የቀበረ ነውና›› እየነገርኩህ ያለሁት ስለምኖርበት የትምህርት አለም ነው፡፡ መርዶውንም ስነግርህ እውቀትን በተስፋ ጠቅልየ ስለቀበርኩ ነው፡፡ በቃ! ማን ያውጋ የነበረ ማን ያርዳ የቀበረ ማለት ይህ ነው፡፡
     ትውልዱ አቅም ሳያንሰው ሁኔታዎች ስላልተመቻቹለትና አርአያ የሚሆን አካል ስለሌለ ብቻ ከንቱ ሆኖ ሲቀር ማየት በጣም ያማል፡፡ አስተማሪም ከተማሪዎች በተወሰነ መልኩ እንኳን መሻል አለበት፡፡ ይህ ካልሆነ ማንን እያዩ ይማራሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ በኢኮኖሚ አቅማቸው ደካማነት ምክንያት መምህራን ለተማሪዎቹ አርአያ መሆን እየቻሉ አይደለም፡፡ መምህር እውቀት ኖሮት ቢሆን እንኳን ተማሪ ብራንድ ጫማ አድርጎ መምህር በሸበጥ ክላስ የሚገባ ከሆነ የሚፈጥረውን ስሜት አስቡት፡፡


     ‹‹ተማር ልጄ ወገን ዘመድ ሃብት የለኝም ከጄ›› ተብሎ እንዳልተዘፈነ ሁሉ ዛሬ መማር መመራመር ሳይሆን መማረር ሆነብን፡፡ ዛሬ ላይ ቀኑ ጨለማ የሆነው ለተማረው የማህበረሰባችን ክፍል ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ስለዚህ ማንን እያየን እንማር?

በማስረጊያነት ትምህርትን ለአገርና ለትውልድ እንዳይጠቅም ማድረግ ከታሪክ ተወቃሽነት በዘለለ ብሄራዊ ወንጀል መሆኑን ዛሬም ነገም እንናገራለን፡፡


Wednesday 2 August 2017

በእንቅርት ላይ ጆሮ ገድፍ፦ የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ መንግስት የሰጠው ማስጠንቀቂያ እና አንድምታው

በአለም አቀፍ የድፕሎማሲ መንደር ለውጥ እየታየ ይመስላል፡፡ በአገር ውስጥ ተቃውሞና ውግዘት እያስተናገደ ያለው የኢት/ያ መንግስት ሰሞኑን በአውሮፓ ህብረት በኩል ተጨማሪ ቢጫ ካርድ ተመዞበታል፡፡ africannews የተሰኘ የዜና አውታር እንደዘገበው የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳዮችና የፀጥታ ፓሊሲ ከፍተኛ ተወካይ የሆኑት Federica Mogherini ለጠቅላይ ሚኒስቴር ሃይለማርያም ደሳለኝ ባስተላለፋት መልዕክት የኢትዮጵያ መንግስት በህገ መንግስቱ ላይ ያሰፈራቸውን ድሞክራሲያዊ እና ሰብዓዊ መብቶች እንዲያከብር ጠይቀዋል፡፡ ይህን ማሳሰቢያ የሰጡት የህብረቱ ተወካይ የአውሮፓ ኮሚሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ጭምር ሲሆኑ አሳታፊ የሆነ የፓለቲካ ድርድር በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማካሄድ ፍላጎት እንዳለና ይሄ ድርድር ደግሞ የራሱ የሆነ የፓለቲካ ምህዳር ይጠይቃል ሲሉ መንግስት በዜጎቹ ላይ የሚጥለውን ገደብ አውግዘዋል፡፡ ("...there was the need to initiate an inclusive political dialogue within the shortest possible time. The dialogue ‘‘will require space, not restriction...") 


 ይህ የህብረቱ አቋም የሚያሳየው የኢት/ያ መንግስት አለም አቀፍ ተቀባይነት አደጋ ላይ እንደወደቀ ነው፡፡ በኢትዮጵያውያን ላይ ዘግናኝ የሆነ ግፍ ሲፈፀም ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ አምባገነኖችን ሳይኮንን የቆየው አለም አቀፉ ማህበረሰብ አሁን ላይ እየነቃ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማትና ድርጅቶች የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ አሳስቧቸው ወደ ኢት/ያ መመልከታቸው መልካም አጋጣሚ ነው፡፡ ሁኔታው በዚህ ከቀጠለም ሌሎች የአለም መንግስታት ተመሳሳይ አቋም ሊያራምዱ እንደሚችሉ ግልፅ ነው፡፡ በዚሁ ሰሞን የልዕለ ሀያሏ አገረ አሜሪካ የፌደራል መንግስት የህግ አውጭ ምክር ቤት ወይም ኮንግረንስ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተመለከተ ውሳኔ ማስተላለፋ ይታወሳል፡፡ ይህ በውሳኔ ቁጥር 128 (Resolution No 128) መሰረት የወጣው መግለጫ ገዥውን መንግስት የሚያስጠነቅቅ ሀይለ ቃልም አለበት፡፡ እንግዲህ የአውሮፓ ህብረቱ ማሳሰቢያ ለኢህአዴግ ሌላ በእንቅርት ላይ ጆሮ ገድፍ መሆኑ ነው፡፡ የህብረቱ ተወካይ ግልፀኝነት የተሞላበት አሰራር ማስፈን ያስፈልጋል በማለት የኢት/ያን መንግስት በአፅንኦት አሳስበዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ መንግስት የዜጎችን ቅሬታ ለመፍታት ቆርጦ ሊነሳ ይገባልም ብለዋል፡፡ ይህ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳይመንት ነው በማለት ለሀይለ ማርያም መናገራቸው ኢህአዴግ በአለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ እንከን እየገጠመውና ድጋፍ እየተነፈገ መሆኑን ያሳብቃል፡፡ ህብረቱ በተወካይቷ በኩል የኢትዮጵያ መንግስት የተዘጋውን የፓለቲካ ምህዳር እንድከፍትና የዜጎችን መሰረታዊ ነፃነቶች እንድያከብር አሳስቧል፡፡ ("She further underlined the need for transparency and determined engagement by the government to respond to the grievances of the population. The EU said it expected the opening up of the democratic space, and respect of fundamental freedoms.") 


ሁለቱ መሪዎች በቀጥታ ስልክ ጭምር የተነጋገሩ ሲሆን ስለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁም ተወያይተዋል፡፡ በህብረቱ በኩል አዋጁ የድሞክራሲ መርሆዎችና የዜጎች ሰብዓዊ መብቶች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል የሚል ስጋት የቀረበ ቢሆንም ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት አይጋፋም ሲሉ አስተባብለዋል፡፡ ("The EU chief expressed concern over the curfew imposed on October 9 and its possible effect on democratic principles and civil rights of citizens. The Prime Minister on his part assured that the state of emergency will not breach human rights protected by the Ethiopian constitution")


ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ማስተባበያቸው የነገሩን መንግስታቸው ከሀድ እንደሆነ ነው፡፡ እውነታው ግን በአገሪቱ ውስጥ ግልፅ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የፍትህ እጦት መኖሩ ነው፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው የፓለቲካ እስረኞች ቁጥርና በገፍ ህይወታቸውን የሚያጡት ዜጎች መበራከታቸው ጭምር ነው፡፡ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሰበብ ያለለምንም ህጋዊ ቅድመ ሁኔታ ዜጎችን ለእስር እየዳረ ያለ ስርዓት ሰብዓዊ መብት አክባሪ ነኝ ሲል እጅጉን ያሳፍራል፡፡

በስተመጨረሻም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የምርጫ ህጉን የማሻሻል ስራ ተጀምሯል ያሉትን መረጃ መሰረት በማድረግ ህብረቱ አስፈላጊ የሆኑ የፓለቲካ ማሻሻያዎች ካልተደረጉ የታሰበው ነገር አላማውን እንደማያሳካ አረጋግጧል፡፡
ዋናው ጉዳይ የኢህአዴግ መንግስት አለም አቀፍ ቅቡልነቱን እያጣ መሆኑ ነው፡፡ ስርዓቱ የሚሻሻል እንዳልሆነ ቢታወቅም የአለም አቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያውያን ላይ ኢህአዴግ እያደረሰ ያለውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት መገንዘቡ ይበል ያሰኛል፡፡


 

ደርብ ተፈራ

Facebook address፦ https://www.facebook.com/teferaderbeee

የፖለቲካ ባህላችን

አየሽ እዚህ አገር ከንቱ ፍረጃ አለ፤ አማኝ ሁሉ አክራሪ፤ ሙስሊሙ አሸባሪ፤ ጉራጌ ቋጣሪ፡፡ ትግሬ ሁሉ ወያኔ፤ ወጣቱ ወመኔ፡፡ አማራው ነፍጠኛ ፤ ደርግ ሁሉ ግፈኛ፡፡ ናቸው እያስባለ ፤ ቁልቁል የሚነዳን ጭ...