Wednesday 30 August 2017

የፖለቲካ ባህላችን

አየሽ እዚህ አገር ከንቱ ፍረጃ አለ፤
አማኝ ሁሉ አክራሪ፤
ሙስሊሙ አሸባሪ፤
ጉራጌ ቋጣሪ፡፡
ትግሬ ሁሉ ወያኔ፤
ወጣቱ ወመኔ፡፡
አማራው ነፍጠኛ ፤
ደርግ ሁሉ ግፈኛ፡፡
ናቸው እያስባለ ፤
ቁልቁል የሚነዳን ጭፍን ጥላቻ አለ!፡፡
(ገጣሚ ዮናስ)
*
‹‹አማራ በሙሉ ጨቋኝ፣ ትምክህተኛ እና የድሮ ስርዓት ናፋቂ አይደለም፣ ኦሮሞው ሁሉ ጠባብ እና የኦነግ ተላላኪ አይምሰልህ፣ ትግሬ መሆን ብቻም በህወሓት (ኢህአዴግ) ጠበቃነት አያስወቅስም፤ የኢህአዲግ አባል አለመሆን ደግሞ ፀረ-ሰላም ተብለን በሻዕቢያ ተላላኪነት ተፈርጀን ዶክመንታሪ እንድሰራብን ሊያደርግ ፈፅሞ አይችልም፡፡››

በኢትዮጵያ የፓለቲካ ባህል ኢህአዴግ ካልሆንክ ተቃዋሚ ነህ፡፡ ተቃዋሚ አይደለሁም ካልክ አንተ የኢህአዴግ ቡችላ ወይም ህዋስ ትባላለህ፡፡ መሀል ላይ ቆመህ የምክንያት ሰው ነኝ ከማንም ጋር የስሜት ቁርኝት የለኝም በማለት የማንም ጠበቃ አልሆንም ኢህአዲግ ሲያጠፋ ከመውቀስ አልመለስም፤ ተቃዋሚዎችም የተሳሳተ ነገር ሲሰሩ እተቻለሁ ብለህ በአቋምህ ብትፀና መሀል ሰፋሪ በሁለት ጥይት ይመታል እንዲሉ ከሁለቱም በኩል ተኩሰው ይመቱሀል፡፡ ምናልባት ከጥቃቱ ተርፈህ ከሆነም ሳትወድ በግድ ፅንፈኛ አቋም እንድትይዝ ጫና ይደረግብሀል፡፡ ለምን ካልከኝ ምክንያቱ ያለኸው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ፓለቲካ በስሜታውያን ፊትአውራሪነት የሚመራ ይመስላል፡፡ ልብ ብሎ ላስተዋለ በአመክንዮ ከሚመሩን ፖለቲከኞች ይልቅ በእውር ድንብሩ የሚጓዙት የስሜት ፈረሰኞችና አስጋላቢዎች ይበልጣሉ፡፡
ማህበረሰባችንም በባህሪው ፅንፈኛ ነው፡፡ ሁለት የአስተሳሰብ ጎራዎች አሉ፡፡ ከነሱ መውጣት አይፈቀድልህም፡፡ ከዚህ ውጭ እሆናለሁ ካልክ በሁለቱም ወገን ትወገዛለህ፡፡

ኢትዮጵያዊ ነኝ አማራ፣ ኦሮሞ ፣ ትግሬ ፣ ደቡብ፣ አፋር ፣ ሱማሌ ፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ወዘተ አይደለሁም ብትል ደግሞ ሁሉም አሽቀንጥረው ሜዳ ላይ ይጥሉሀል፡፡ ወፍ ዘራሽ ተብለህ ተቆርቋሪ፣ ጧሪና ቀባሪ ታጣለህ ማለት ነው፡፡ ይህ ሁሉ የኢትዮጵያ ወቅታዊ የፓለቲካ ናዳ ነው፡፡ ዘረኝነት ስሩን የሰደደበት ፓለቲካችን አገራዊ ስሜትን መሸርሸር ጀምሯል፡፡ ይህ ብቻ አይበቃቸውም! ኢትዮጵያዊነት ደሜ ነው ብለህ ስትዘምር ደምህን ለማፍሰስ አሰፍሰፈው ይመጡብሀል፡፡ አንዱን ፊት ለፊት ስትጋፈጥ ሌለኛው ጥቃት ያደርስብሀል፡፡ የፓለቲካ ባህላችን በወዳጅነትና ጠላትነት ላይ የተመሰረተ ነውና ጥቃቱን መቋቋም አቅቶህ ፅንፍ ልያዝ ብትልም ጥላቻው አይለቅህም፡፡ ወይ ከኛ አልያም ከነሱ አይነት ባህሪ የፖለቲካ ጨዎታችን መገለጫ ነው፡፡ መሐል ላይ ብትሰፍር በግራም በቀኝም የመከራ ጥፊ ትቀምሳለህ፡፡ ሳትወድ በግድ ጥግ መያዝ አለብህ፡፡

የእኔ የምትለው ድርጅት ችግር ካለበት መተቸት ግድ ይልሀል፡፡ ካልሆነ ግን ለውድቀቱ እየሰራህ መሆኑን አትዘንጋ፡፡ እኛም መከተል ያለብን ድርጅቶችን ብቻ ሳይሆን እውነትን፣ ነፃነትና ፍትህን ነው፡፡ አንተን ያቀፈህ ድርጅት ህዝባዊነት ከሌለው ራስህን መነጠል ታላቅነት እንጅ ቂልነት አይደለም፡፡ የእነርሱ የምትለው ድርጅት መልካም ነገር ከሰራ ድጋፍ ብታደርግ አዋቂነት ነው፡፡ ስለዚህ መሀል ላይ ሁን፡፡ በነፈሰት አብረህ አትንፈስ፡፡ ስማኝ ወገኔ! ፅንፈኛ አትሁን፡፡ አርስቶትል ‹‹ወርቃማው አማካይ›› የሚለው ሌላ አስተምህሮ አለው፡፡ ወርቃማው አማካይ ላይ መሆን ቅቡልነትን እና ትክክለኛ ስብዕናን መወከሉንም ልብ ይሏል፡፡ ስለዚህ እኔ የምልህ ፍልስፍናዊ መሰረት ያለው ነው፡፡ ውኃ የማይቋጥር አሉባልታ አይምሰልህ፡፡ ሁሉም ነገር በመጠኑ ሲሆን ጥሩ ነውና ጫፍ ላይ አትመሽግ፡፡ የሁለቱንም ፅንፍ ምንነት ተገንዝበህ አመዛዝነህ መሀል ላይ ስፈር (ወርቃማው አማካይን መፈለግህን አትርሳ)፡፡ ቀይ ካልሆነ ጥቁር ነው አትበል፡፡

የኛ ማህበረሰብ በሎጅክ ላይ ተመስርተህ ስህተቱን ከምትነግረው ይልቅ ጥቃቅን ስኬቱን አንስተህ ብታሞግሰውና ብታወድሰው ይመርጣል፡፡ ማህበረሰባችን የሚፈጥራቸው የፖለቲካ ድርጅቶችም ከዚህ ልማድ እስር አልተፈቱም፡፡ ቡድንተኝነት መገለጫቸው ነው፡፡ ልማታዊ ድሞክራት ነኝ ለሚል ድርጅት ኒዮ-ሊበራሊዝም ጭራቅ መስሎ ይታየዋል፡፡ ዜጎቹን የኒዮ-ሊበራል አቀንቃኝ እያለም መውጫና መግቢያ ያሳጣል፡፡ ‹‹ከመጠምጠም መማር ይቅደም›› እንዳሉት አፄ ቴዎድሮስ ኒዮ-ሊበራል ብሎ ሰዎችን ከማሳቀቃችን በፊት ስለ ርዕተዓለሙ ጥልቅ እውቀት ሊኖረን ይገባል፡፡ ይህን ያልኩት አንዳንድ ደናቁርት ካድሬዎች ኔዮ-ሊበራሊዝምን ‹‹ውጉዝ ከመአርዮስ›› እያሉ በጭፍን ሲተቹና ሲያወግዙ በማስተዋሌ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ልማታዊ መንግስትን አለመገደፍ የኔዮ-ሊበራል ታፔላ አስለጥፎ ከርቸሌ የሚያስወርድበት ፖለቲካዊ እንቆቅልሽ አልገባህ ብሎኛል፡፡

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል አዳምና ሄዋን በሰሩት ስህተት የሰው ዘር በሙሉ የቅጣቱ ሰለባ እንደሆነው ግለሰቦች ባጠፉትና በእነሱ ሀጥያት ቡድኖች የመከራ ገፈት ሲቀምሱ ማየታችን የተለመደ ነው፡፡ ልክ እንደነ አዳም ታሪክ የኛም የጎሳ ፖለቲካ ‹‹አንድ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ…ወዘተ ባጠፋው ጥፋት ሚሊዮኖች ዋጋ እንድከፍሉ እያስገደደ ነው፡፡›› አንዳንዴ በኦሪት ህግ የሚመራ ረጅም የፓለቲካ ጉዞ የጀመርን ይመስለኛል፡፡ ለመሆኑ ‹‹የአባት እዳ ለልጅ የእማየን ለአባየ አይነት የፖለቲካ ጫወታ ያዋጣን ይሆን?›› እኔስ እልሀለሁ አያዋጣንም፡፡ ‹‹በላይነህ በሰራው ስህተት ደመላሽ መቀጣት የለበትም፤ ኃጎስ በፈጠረው ችግር ገብረእግዚዓብሄር ሊጠየቅ አይገባም፤ መገርሳ ባጠፋው ዱጋሳ አይወቀስም ሊወቀስም አይገባም፡፡›› በወንጀለኛ መቅጫ ህግም የወንጀል ድርጊት ተጠያቂነት በዝምድና ብቻ ከአንዱ ወደ ሌላ አካል ፈፅሞ አይተላለፍም፡፡ በፖለቲካው ዓለም በጅምላ መወንጀሉ መቅረት ያለበት ህጋዊና ሞራላዊ መሰረት ስለሌለው ነው፡፡ የችግሩ ፈጣሪ እስካልሆን ድረስ ‹‹ከኑግ ጋር የተገኘሽ መጭ አብረሽ ተወቀጭ›› በሚለው እሳቤ የሌለብንን እዳ ልንከፍልም አይገባም፡፡ ማንም ሰው በስማበለው የአጥፊው ወገን ስለሆነ ባልሰራው ወንጀል በመሰለኝና በደስአለኝ መንገድ በመሄድ መቀጣት የለበትም፡፡

የመንጋ አስተሳሰብ የትስ ያደርሰን ይሆን? አላቅም! እኔ ካጠፋሁ ተወቃሹ እኔና እኔ ብቻ ነኝ፡፡ በእኔ ወንጀል ማንም ሰው ሊከሰስ አይገባውም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚያሳዝን ሁኔታ ግለሰቦች በመንጋ ጭንቅላት የሚያስቡት ወደው አይመስለኝም፡፡ ተገደው ነው ፤ ለደህንነታቸው ሲሉ! መሀል ላይ ቢሰፍሩ የሚደርስባቸውን ጫና ያውቁታልና ፅንፍ ይይዛሉ፡፡ ለሶስተኛው አማራጭ ብሎም ለግለሰቦች ልዕልና ቦታ ከሰጠን ግን የፓለቲካ ደዌውም ይለቀናል፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ ሰዎች ደጋፊዎቻችን ካልሆኑ ለምን ለኔ አታጨበጭቡም ብለን በጠላትነት እንፈርጃቸዋለን፡፡ ፍረጃው ግን መሰረተ ቢስ ነው፡፡ ለኛም መሻሻል አይጠቅምም፡፡
እኛ አገር የተሻለ ሀሳብን ሳይሆን ቡድኖችን እንድትከተል ትገደዳለህ፡፡ ይህ አካሄድ እውነትን መጨቆን ነው፡፡ ሁሉም ነገር ከምክንያት ይልቅ በስሜት መነፅር መታየት ይጀምራል፡፡ ነገር ግን ምንም ለውጥ አያመጣም፡፡

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ መሀል ሰፋሪዎች ቦታ ቢሰጣቸው ጫፍና ጫፍ ቆመው የተፋጠጡትን ወገኖች በመጠኑም ቢሆን ማስተካከል ይቻል ነበር…ባይሰበር፡፡ መሀል ላይ አስታራቂና ከስሜት የራቀ አካል ከሌለ ተያይዞ የፖለቲካ ሲዖል ውስጥ መግባት ነው፡፡ አጥፍቶ የመጥፋት ፖለቲካ ማለትም ይህ ነው፡፡ ከነችግራችን ልንደገፍ ይገባል ማለት ከችግሩ መውጣት ብሎም ችግሩን ማወቅ አንፈልግም ብሎ ማሰብ ነው፡፡ ሰው ስራ ሲሰራ ይሳሳታል፣ ስህተቴን ለምን ነገራችሁኝ ብሎ ዘራፍ ማለት ግን ከሰውኛ ማንነት መውረድ ነው፡፡ ለለውጥ ከተነሳን አጨብጫቢ ብቻ ሳይሆን የሚተቸን አካል ያስፈልገናል፡፡
አንድ ከብርሃኑ ሞላ ነጠላ ዜማ ላይ የሰማኃት የግጥም ስንኝ ሁኔታውን የበለጠ ስለገለፀችልኝ እንካችሁ ብያለሁ፡፡
አንድ ሰው በአንድ አገር ሲኖር ብቻውን፤
ሳያውቀው ይኖራል የገዛ ነውሩን፡፡
ነውሬን የሚነግረኝ አንድ ወንድም አጥቼ፤
በአመቱ አገኘሁት ለፍቼ ታክቼ፡፡

ስሜታዊነት የኢትዮጵያ ፖለቲካ አልፋና ኦሜጋ መሆኑን ለማወቅ መሀል ሰፋሪዎች ይዞታ ማጣታቸውንና የብዙዎቻችን ነፍስ በዘረኝነት መስከሯን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ለካ ዘረኝነት ልኩን ሲያልፍ ነፍስንም ሳይቀር ያሰክራል፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ያውም ሉላዊነት (Globalization) አለምን ወደ አንድ መንደር ለመጠቅለልና ግሎባል ዜግነት ያለው ትውልድ ለመፍጠር ዳር ዳር እያለ ባለበት ወቅት ኢትዮጵያውያን ከጎሳ ዘንቢል መውጣት አለመቻላችን እጅጉን ያስቆጫል፡፡ ወደድንም ጠላንም እኛ እርስበርስ ስንናከስ ዓለም በጠንካራ የኢኮኖሚ ክንዷ ገፍታ ከጫወታ ውጭ ታደርገናለች ፤ አድርጋናለችም፡፡ የፉክክር በራፍ ሳይዘጋ ያድራል ማለት ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡

እዚህም እዚያም በዘረኝነት የሰከሩ ነፍሶች ሲራወጡ ማየት ተስፋ ያስቆርጣል፡፡ በዘረኝነት የሰከሩ ነፍሶች ሳያጠፉ አይጠፉም፡፡ ዘረኝነት ነፍስን በካይ ጋዝ ነው፡፡ ዘላለማዊነት ያላትን ነፍስ ስሜት ሲያኮላሽብህ ቆመህ ማየት የለብህም፤ ከራስህ ጋር ታግለህ ስሜትን ድል መንሳት ይኖርብሀል፡፡ የስሜት ፈረሰኞችንም በፅናት ልትታገል ይገባል፡፡ ወገኔ ‹‹ነፍስህን አታቆሽሽ›› አደራ! መሪዎች ያልፋሉ የጥላቻ መርዛቸው ግን ይቅር ባይ ልብ ከሌለን አብሮን ይዘልቃል፡፡ እንደ ጎርፍ የሚያልፉት መሪዎች የጥላቻ ደለላቸው እንዳይውጠን በመከላከል ራሳችንን መታደግ ያለብን እኛው ነን፡፡

ህዝብ ለህዝብ በጥላቻ መስኮት እያጮለቀ እንድተያይ ማድረግ ታሪክ በመጥፎ ምዕራፍ እንድያስታውሰን መፍቀድ ነው፡፡ አሁን ያለው የአገራችን ፓለቲካ አንዱ በሌላው ላይ ተነስቶ አንገት የሚቀነጥስበትን ሰይፍ ያዘጋጀልን ይመስላል፡፡ የሚመሩን አካላት ፍቅርን ወደ ጎን ትተው በጥላቻ መንገድ መጓዝ ከጀመሩ ሰፊው ህዝብ በነፈሰበት ስለሚነፍስ ላንመለስ ወደ ጨለማው ሄደን እንቀራለን፡፡ የህዝቡ ንቃተ ህሊና የተሻለ ካልሆነ ውቃው ደብልቀው ሲባል አብሮ መጨፈሩ አይቀርም፡፡

ብሄራዊ መግባባትን መፍጠርና አንድነትን ማምጣት ከባድ የፖለቲካ አሳይመንት ነው፤ የጥላቻ መርዝን መርጨት ግን በጣም ቀላል ነው፡፡ ደካሞች ጥላቻን ሲዘሩ ተባባሪዎቻቸው አጭደው ይወቃሉ፤ ጠንካራና እውነተኛ የህዝብ ልጆች ግን ለፍቅርና አንድነት ይሰራሉ፡፡ ደናቁርት ዘረኛ ሲሆኑ የበሰሉትና ምክንያታዊ የሆኑት ግን የአንድነት ዜማን ያዜማሉ፡፡ ቁሳዉያን ዘረኝነትን ሲያነግሱ መንፈሳዉያን አንድነትን ይሰብካሉ፡፡ ለሆዱ ያደረ ባለስልጣን ህዝብን ሲከፋፍል፤ እውነተኛ ህዝባዊነት ያለው ግን የዘረኝነት እሳት ላይ የአንድነት ውኃ ይቸልሳል፡፡ የተማረው መሀይም ጠባብ ሲሆን የእውቀት አዝመራን የወቃው ግን ከአገርም አልፎ ለአለም ይጨነቃል፡፡

‹‹ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል ሁሌም እንደደማ ይኖራል›› እንድሉ ከዘረኞች ጋር ለመኖር ዘረኛ መሆን ግደታ ሆኖ ሲመጣብህ የሞቀ አቀባበል ካላደረክ የፅንፈኞች ጥቃት ሰለባ ትሆናለህ፡፡ መግቢያና መውጫም ያሳጡሀል፤ ቢሆንም! እመነኝ! ዘረኛ ሆኖ ከመገኘት በዘረኞች የጥላቻ ብትር መደብደብና መሰቃየት ይሻላል፡፡ እነሱ ቢያሰቃዩህ ስጋህን ቢጎዱት እንጅ ነፍስህ ምንም አትሆንም፡፡ አንተ ብትደማ፣ ብትቆስልና ብትቆሽሽ ነፍስህ ንፅህት ናት፡፡

ሁሌም ኢትዮጵያዊነቴ አለፍ ሲልም ሰው መሆኔ እንጅ የመጣሁበት ክልል ለኔ ምኔም አይደለም፡፡ አማራው ሲበደል ያመኛል፣ ኦሮሞው ጥቃት ሲደርስበት ህመሙ ይሰማኛል፣ ትግሬና ደቡቡ፣ አፋሩና ሱማሌው፣ ቤኒሻንጉሉ እና ጋምቤላው እንድሁም ከሐረር የመጣው ሲከፋው አብሮ ይከፋኛል፣ እንቅልፍም ይነሳኛል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም! ድንበር ዘለል የሆኑ የሰው ልጅ ስቃዮች ያሳስቡኛል፡፡ እዚህ ሁኜ መካከለኛው ምስራቅ ያለው ብጥብጥ ሰላሜን ይነሳኛል፡፡ እኔ ስለ መካከለኛው ምስራቅ ቀውስ አላስብም ብየ እንኳን ባስብ አለማሰቤ ቀስቅሶ ያሳስበኛል፡፡ ለምን ብለህ ከጠየከኝ እነሱም በአንድየ አምሳል የተፈጠሩ ሰዎች ናቸው የሚል ምላሽ አዘጋጅቸልሀለሁ፡፡ ዘር ለገበሬ ነው ሲሉ ሰምተህ ከሆነ ያልኩት ይገባሀል፡፡ የሰው ልጅ አንድ እንጅ የተለያየ ዘር የለውም፡፡ በመልክና በባህርይ ብንለያይ እንኳን ደማችን አንድ ነው፡፡ ነጭ ደም ያለው ካለ እኔ ደሜ ቀይ ነውና አሁኑኑ ዘረኛ እሆናለሁ፡፡
በዘረኝነት መርዝ የተለወሰ ፅንፈኛ የሆነ ጥላቻ አዘል ፖለቲካ አገርን ያፈርሳልና በእስካሁኑ ይብቃን፡፡

No comments:

Post a Comment

የፖለቲካ ባህላችን

አየሽ እዚህ አገር ከንቱ ፍረጃ አለ፤ አማኝ ሁሉ አክራሪ፤ ሙስሊሙ አሸባሪ፤ ጉራጌ ቋጣሪ፡፡ ትግሬ ሁሉ ወያኔ፤ ወጣቱ ወመኔ፡፡ አማራው ነፍጠኛ ፤ ደርግ ሁሉ ግፈኛ፡፡ ናቸው እያስባለ ፤ ቁልቁል የሚነዳን ጭ...