Wednesday 14 June 2017

"ከኖርንም አብረን ሞትም ከሆነ ተያይዘን"--- የአባይ ጉዳይ (By Derbe Tefera)

ያለነገር ግብፅ እንደ አሞራ አልዞረችንም፡፡ የውኃ ፓለቲካው ጤነኛ አይደለም፡፡ ሲፈልጉ እንተባበር ይላሉ ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ  Either we live or die together የምትል ማስፈራሪያ አዘል መልዕክት ይልኩብናል፡፡ ምን ተሻለ?
 ነገርን ነገር ያነሳዋልና የውሃ ጉዳይ ከተነሳ እኛ ኢትዮጵያን ሁለት ትዝታዎች አሉን ፦
✔የንግስት ሳባ ውሃ ጥማትና በንጉስ ሰሎሞን መደፈር ፤
✔የእንዳየሱስ ምንጭ እና የእቴጌ ጣይቱ የማይረሳ አስደናቂ ፀረ-ፋሽስት ቀመር፡፡ የታሪክ አባቱ ሄሮዳተስ (The fatherof History) እንዳለውና ብዙዎች እንደሚያስቡት ግብፅ "የአባይ ወንዝ ስጦታ" ተደርጋ ትወሰዳለች፡፡ (....the gift of Nile").
ኢትዮጵያም "የአፍሪካ የውሃ ማማ" እንደመሆኗ መጠን ለወንዙ ከ85% በላይ ውኃ ትገብራለች፡፡ እናም የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት በአባይ ላይ የተመሰረተ ተፈጥሯዊ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ለዛም ይመስላል "ከኖርንም አብረን ሞትም ከሆነ ተያይዘን" የሚለው ድስኩር በውኃ ድፕሎማሲው ተደጋግሞ የሚሰማው፡፡

በፈረንጆቹ አቆጣጠር 2011 የግብፅን ታሪካዊ ነገር ግን አግባብ ያልነበሩና በቅኝ ግዛት ወቅት የተፈረሙ ስምምነቶችን ዋጋ የሚያሳጣ ለግብፃውያኑ የራስ ምታት የፈጠረ ግድብ መሰረት ድንጋይ ጉባ በረሃ ላይ ተጣለ፡፡ በወቅቱ የነበረው ሁኔታ ለፅሁፌ ፍጆታ እምብዛም ስለማይጠቅመኝ ወደ ቅርብ ክስተቶች ልመለስና ከዛም ራቅ ብየ ወደ 19 ኛውና 20ኛው ክፍለዘመን ስምምነቶች እወስዳችኃለሁ፡፡ የግብፅ ባለስልጣናት በተለያየ ጊዜ የተለያየና እርስ በርስ የሚጋጭ የፓለቲካ አቋማቸውን በሚድያም ሆነ በሌሎች የመገናኛ መረቦች አሰምተውናል፡፡

ከአል ሲሲ ወደ ስልጣን መምጣት ጋር ተያይዞ የተወሰኑ ለውጦች በውሃው ፓለቲካ ላይ የታዩ ይመስላል ፤ ነገር ግን የግብፅ ወደ አፍሪካ ቀንድ ጠጋ ጠጋ ማለት አንድምታው በአግባቡ መተንተን አለበት፡፡ እንግሊዛውያን በአንድ ወቅት "አባይን የተቆጣጠረ፡ ግብፅን ተቆጣጠረ( The One who controls Nile-controls Egypt") ብለው ነበር ፤ እናም ግብፃውያንም በተቃራኒው እንድህም አለ ወይ በማለት አባይን ከተቆጣጠርን ማን ይነካናል ሳይሉ አይቀርም፡፡ በዘንድሮው አመት ለአካዳሚክ ጉዳይ ግብፅ ሄጀ ነበር፡፡ በነበረኝ የቀናት ቆይታ የተገነዘብኩት ነገርም የተደበላለቀ ስሜት ፈጥሮብኛል፡፡ በአንድ በኩል ችግሩ የመንግስታት ክፍተት የፈጠረው ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ስር የሰደደ አለመተማመን በሁለቱ አገራት ህዝቦች መካካከል እንዳለ ያስገነዝባል፡፡ በዋናነት የተረዳሁት ግን የአባይ ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶት አገራዊ ጥቅምን ለማስከበር መንቀሳቀስ እንዳለብን ነው፡፡
.
በብሪታንያ እና ጣሊያን መካከል የተካሄደውን የ1891 ሰምምነት እንተወውና በአፄ ምኒልክ ዘመን አድስ አበባ ላይ በኢትዮጵያ እና ታላቋ ብሪታኒያ መካከል በ1902 የተካሄደው ስምምነት አንቀፅ 3 ን ብንወስድ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ውሃ ላይ የመጠን ለውጥና ቅነሳ ሊያደርስ የሚችል ፕሮጀክት እንዳትገነባ የሚከለክል ነበር፡፡ የ 1929 እንዲሁም የ1959 ስምምነቶችን ብናይ የኢትዮጵያን ፍላጎት ወይንም  ፍትሃዊ የአባይ ወንዝ ተጠቃሚነትን ያገናዘበ አልነበረም፡፡ በመሆኑም የበይ ተመልካች ሆነን ቆይተናል፡

እዚህ ላይ ወደ ቅርብ ኩነቶች እንመለስና ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለቱን አገራት ያቀራርባል ወይንስ እርስ በርስ በጥርጣሬ ሰባራ መነፅር እንድተያዩ ያደርጋል? የሚለው ጥያቄ ማጤን ወሳኝ ይመስለኛል፡፡

አንዳንድ ተንታኞች ለግብፅ የአባይ ጉዳይ የህልውና ጉዳይ ስለሆነ ምላጭ መሳቧ አይቀርም ይላሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች የግብፅን ወደ አፍሪካ ቀንድ ጠጋ ጠጋ በማለት ወታደራዊ መቀመጫ ማፈላለግን እንደ ምሳሌ ያነሳሉ፡፡ በበኩሌ ጉዳዩ የሁለቱ አገራትን ግንኙነት አደጋ ላይ አይጥልም ማለት አልችልም፡፡
ግብፃውያን በዓለም አቀፍ ድፕሎማሲ ጦርነት የተለያዩ አገራትን ድጋፍ አስነፍገውናል፡፡ አሁን ላይ ደግሞ የሰይጣን ጆሮ ይደፈንና  መሳሪያ እንምዘዝ ካሉ ተጎጅው ማን ሊሆን ይችላል ብለን ብናስብ፦
1. በዓለም ላይ በውሃ ምክንያት የተደረጉ ጦርነቶች ጥቂት መሆናቸው ወደፊት ግን ተንታኞች "The future war will be over water" እንደሚሉት አይሆንም አልልም ፤ የውሃ ፍላጎት መጨመር ፤ የህዝብ ብዛት እና ድርቅ ችግሩን ሰላባባሰው ፤
2.ሱዳን ከጎኗ ካልሆነች ግብፅ ወታደር ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ማስጠጋት አትችልም፡፡ ነገር ግን አህጉር አቋራጭ የጦር ጀቶችን ልትጠቀም ትችላለች፡፡
3. ኢትዮጵያ አምደ ፂዩን አግደዋለሁ ብሎ የሃይማኖት ትርፍ እንዳገኘበት ዛሬ ላይም  ወንዙን ብዛት ያላቸው እስከ 20,000 የሚደርሱ ትናንሽ ግድቦች በመገንባት የውሃ ፍሰት ማቆም ስለምትችል ፤
4. ግድቡ ካለቀ ከግብፅ አሜሪካ ሰራሽ F16  ጀቶች በበለጠ ለጥፋት ስለሚያገለግል ፤ ውሃው ቢለቀቅ ሱዳንን ጨምሮ ግብፅን በጎርፍ ስለሚያጥለቀልቅ ፤
5. የሁለቱ አገራት ህዝቦች ታሪካዊ ትስስር (የሃይማኖትና ባህልን ጨምሮ) ስላላቸው ፤ እና ሌሎች ባልተጠቀሱ ጉዳዮች ምክንያት ጦርነቱ ኪሳራ እንጅ ትርፍ አይኖረውም፡፡ በእርግጥ "GLOBAL FIRE INDEX" የተሰኘው ተቋም ግብፅን በወታደራዊ አቅም ከአፍሪካ ቀዳሚ አድርጓታል ፤ ኢትዮጵያ በ 3ኛነት ተቀምጣለች፡፡ ከዚህ ወጣ ስንል የግድቡን ተፅዕኖና የሁለቱን አገራት የአባይ ወዳጅነትና-ጠላትነት እንድሁም የወደፊት "WATER SECURITY DILEMMA"ን በተመለከተ የተለያዩ አካላት ትኩረት ሰጥተው ካልሰሩ የውኃ ፓለቲካው ለተፋሰሱ አገራት ደም አፋሳሽ መንስዔ መሆኑ አይቀርም፡፡


መስቀለኛ መንገድ ላይ ያለች አገር-- "ኢትዮጵያ"

እንረስ ካላችሁ ተስማምተን እንረስ ፤
አይሆንም ካላችሁ ተውት ዳዋ ይልበስ፡፡
.
ወቅታዊ የአገራችን ሁኔታ እጅጉን አሳሳቢ ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያ ከማትወጣበት የጥላቻ ፓለቲካ ባህር ውስጥ ገብታለች፡፡ የዘውግ ፌደራሊዝሙ የታሰበለትን አላማ ሊያሳካ አልቻለም፡፡ ይባስ ብሎ በእሳት ላይ ነዳጅ መጨመር ሆኗል፡፡ ሁሉም የአገሪቱ ዜጋ ኢትዮጵያን ማስቀደም ሲገባው ወደ ጎሳ ዘምቢል ራሱን እየጨመረ ነው፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወድህ እየተስተዋሉ ያሉ እንቅስቃሴዎች ኢትዮጰያ እንደ አገር የመቀጠል ተስፋ ላይኖራት ይችላል ያስብላሉ፡፡ በፅንፈኝነት ላይ የተመሰረተው ፓለቲካችን ፍሬ አፍርቶ ህዝብ ለህዝብ በጥላቻ መስኮት እንድተያይ አስችሏል፡፡ ይሄ ነገር ወደ እርስ በርስ እልቂት መውሰዱም ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡
በስልጣን ላይ ያሉት አካላትም ለአገራዊ ጥቅም ደንታ የላቸውም፡፡ <<ስለሞትን እንገዛለን>> በሚል አስተሳሰብ የስልጣን ጥማቸውን ለማርካት ህዝብን ከፋፍለው ለመግዛት የነደፋት የስልጣን ማቆያ ፕሮጀክት ትርፋማ ሆኗል፡፡ ዛሬ ላይ ከምክንያት ይልቅ ስሜት በአገራችን የፓለቲካ ሰማይ ነግሷል፡፡ በስሜት የሚመራ የፓለቲካ ማህበረሰብ ደግሞ እርስ በርሱ ይናከሳል፡፡ መንግስትን እንቃወማለን የሚሉ ግለሰቦች ፣ ቡድኖች እና የፓለቲካ ፓርቲዎች ሳይቀሩ በአመክንዮ ሳይሆን በደመነፍስ ሲንቀሳቀሱ ማየት እጅጉን ያበሳጫል፡፡ በስልጣን ላይ ያለው ወገን ከዙፋኑ ቢወርድ እንኳን <<ሌባ ሲሰርቅ ይስማማል ሲካፈል ይጣላል>> እንዲሉ ጤነኛ አስተሳሰብ የሌላቸው አንዳንድ የነፃነት ታጋይ ተብየዎች ተስማምተው አገር ያስተዳድራሉ ለማለት የሚያስችል ተጨባጭ እውነታ የለም፡፡ እነሱ ከመንግስት የሚለዩት ቤተ መንግስት ስላልገቡ ብቻ ነው ለማለት ያስደፍራል፡፡ ጉልቻ ቢላወጥ ወጥ አያጣፍጥም አይነት ነው ነገሩ፡፡
አንዳንድ ቡድኖችማ ጭራሹኑ ግልፅ የሆነ የፓለቲካ አቋም ብሎም ርዕዮተ ዓለም የላቸውም፡፡ ይቃወማሉ ግን ለምን ምን አላማ እንግበው እንደሆነ ግልፅ አይደለም፡፡ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው ማለት ይሄኔ ነው፡፡
ከሁሉም የበለጠውና አሳሳቢው ጉዳይ ግን የጥላቻ ፓለቲካችን መዘዝ ነው፡፡ በዚህ ከቀጠልን ማየት የማንፈልገው መጥፎ ነገር ይፈጠራል፡፡ በኦሪት ህግ የሚመራው የአገራችን ፓለቲካ ጥፋት አርግዟል፡፡ በመንግስት ሰፓንሰር የሚደረገው ይህ ጥላቻ አዘል አካሄድ አገር ያጠፋልና አስቸኳይ መፍትሔ ይሻል፡፡
ህዝብ ለህዝብ መተባበር ካልቻለ ሁሉም ነገር ቀሪ ነው፡፡ አገር ዳዋ ለበሰች ማለት ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ አገራዊ መግባባት እስካልተፈጠረ ድረስ የስርዓት ለውጥ ቢደረግ እንኳን ኢትዮጵያ ከፓለቲካ ደዌ አትድንም፡፡
.
በአመክንዮ የሚመራ ማህበረሰብ እንፍጠር!

የፖለቲካ ባህላችን

አየሽ እዚህ አገር ከንቱ ፍረጃ አለ፤ አማኝ ሁሉ አክራሪ፤ ሙስሊሙ አሸባሪ፤ ጉራጌ ቋጣሪ፡፡ ትግሬ ሁሉ ወያኔ፤ ወጣቱ ወመኔ፡፡ አማራው ነፍጠኛ ፤ ደርግ ሁሉ ግፈኛ፡፡ ናቸው እያስባለ ፤ ቁልቁል የሚነዳን ጭ...