(መግቢያ ቢጤ) ገዢው ፓርቲ ገና 4 ኪሎ ቤተመንግስት ሲገባ ነበር የፊታችሁ ቀለም አላማረኝም በሚያስመስል አይነት ደካማ አመክንዮ ለምን ጠየቁኝ እኔ የምላቸውን አምነው አይቀበሉም ወይ ታሪክ ለኛ ሊያስተምሩ የሚችሉበት አግባብም የለም በማለት ነበር ምሁራንን ከአንጋፋው የአድስ አበባ ዩኒቨርስቲ ያባረረው፡፡
አድስ የፈጠራ ታሪክ እናስተምራችሁ አዳምጡን ማድመጥ ካልቻላችሁ ግን ብቃት የላችሁም ዩኒቨርስቲውን ለቃችሁ ትወጣላችሁ አይነት የሚመስል ማስፈራሪያ ነበር ነገሩ፡፡ የተባረሩት ምሁራን ቁጥር ወደ 40 ይጠጋል፡፡ አብዛኞቹ ወደ ውጭ አገር ኮበለሉ፡፡ ኮብልለውም በግለሰብ ደረጃ ተጠቀሙ እንጅ አልተጎዱም፡፡ አገሪቱ ግን አንጋፋ ምሁራኖቿን ነበር በወቅቱ ያጣችው፡፡
The Ethiopian Herald የተሰኘው ጋዜጣ "Ethiopia's face of brain drain: Leaving while productive, returning as retirees" በሚል ንዑስ አርዕስት ስለ ምሁራን ስደት ሰሞኑን መዘገቡ ይታወቃል፡፡ ENN ቴሌቪዥንም በዚሁ ጉዳይ ላይ ዳጉ በተሰኘ ፕሮግራሙ (ሄራልድን አጣቅሶ) ሽፋን ሰጥቶ ነበር፡፡ ነገር ግን ከተወያዮቹ መካከል አንደኛው ጋዜጠኛ የችግሩ መንስኤ "ኢኮኖሚያዊ ነው" ብሎ የደረሰበት ድምዳሜ ህፀፅ አዘል ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ ምክንያቱም ለአብነት ያክል 40ዎቹን የእውቀት አዝመራ ባለቤቶች ጭምር ያሰደደው ድህነት አይደለም፡፡ ስንቱ ምሁራን ናቸው አገራቸውን ማገልገል እየፈለጉ መንግስት እግራቸውን የቆረጣቸው፡፡ የአካዳሚክ ነፃነት በሌለበት አገር እንኳን የወጡት ሊመለሱ አገር ውስጥ ያለውም መውጫ ቀዳዳ ፈላጊ ነው፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ ደምወዝ ስላነሰ ብቻ ሳይሆን የመንግስት ጉንተላ አላስቀምጥ ስላላቸው ነው፡፡
ለምሳሌ ያክል የአድስ አበባ ዩኒቨርስቲ ድምቀት የሆኑትን ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋና ዶ/ር መረራ ጉድናን ማንሳት ይቻላል፡፡ አንቱ የተባሉት እነዚህ ሁለት የእውቀት አባቶች በገዥዎች የተነሳ ዋጋ እየከፈሉ ነው፡፡ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ከሚወደው የመምህርነት ሙያ ተመንጭቆ 6 ኪሎን ለቀህ ውጣ ሲባል ዶ/ር መረራ ደግሞ ከርቸሌ ሆኗል እጣው፡፡ ሁለቱ ምሁራን ሚዛናዊ በሆነ ትችት ነው የሚታወቁት ነገር ግን እኛ ብቻ ነን አዋቂ ማጨብጨብ እንጅ ወደኛ ትችት መሰንዘር ወንጀል ነው ተብለው የግፍ ሰለባ ሆኑ፡፡ ስለዚህ እውነት ጋዜጠኛው ከልቡ ነው የተናገረው ወይስ መንግስትን ላለማስቀየም ነው? ብለን መጠየቁ ትክክል ነው ባይ ነኝ፡፡ እንዲህ አይነት ትንታኔ ከጋዜጠኝነት ስነምግባር ያፈነገጠ ወገንተኝነት ነው፡፡
በአገር ፍቅር ስሜት የነደዱ ስንት ምሁራን በአለም አቀፍ ደረጃ እንደ ጨው ተበትነው ቀርተዋል፡፡ አንዳንዶችማ በየ ሚድያዎች ምኞታችን አገራችንን ማገልገል ነው ሲሉ ሆድ ያስብሳሉ፡፡ ይህ ምኞታቸው እንኳን ደህና መጣችሁ ብሎ የሚቀበል መንግስት ባለመኖሩ ምክንያት እንደጉም ተነነ፡፡ ለአገር አሳቢ መንግስት ቢኖረን ኖሮ "ቀይ ምንጣፍ አንጥፎ በፓሊስ ኦርኬስትራ የታጀበ አቀባበል" ይደረግላቸው ነበር፡፡
የምሁራን ፍርጠጣ እልባት ካልተሰጠው ዩኒቨርስቲዎቻችን እንደ ንብ አልባ ቀፎ ባዶ መቅረታቸው ግልፅ ነው፡፡
ንቡ ሄደ ኧረ ንቡ ሄ፤
አገጣውን ጥሎ ፤
ከአንዱ አገር አንዱ አገር፤
ይሻለኛል ብሎ፡፡
...ሲል ንቡ የሄደበት የአማራ ገበሬ እና አናቢ እንዳንጎራጎረው ዩኒቨርስቲዎችም የምርምርና እውቀት አገጣቸው ብቻ እንዳይቀር ያስፈራል፡፡
ማንም ተጨቁኖ መኖር አይፈልግም፡፡ የተሻለ ደመወዝ ባይሰጣቸው እንኳ ተፈጥሯዊ ፀጋ የሆነውን ነፃነት ሊነፈጉ አይገባም፡፡ ስለዚህ ለምሁራን ፍርጠጣ ዋናው ችግር ኢኮኖሚያዊ ብቻ ሳይሆን ፓለቲካዊም ጭምር ነው፡፡ ዋናው እና አነሳሽ ምክንያቱ (Major and triggering cause) ኢኮኖሚያዊ ነው ማለት የደከመ አመክንዮ ነው፡፡ ፍረጃ (Hasty Generalization) አይነት ህፀፅ ስለሆነ ሊታረም ይገባል፡፡ M. Twain "It is easier to fool people than to convince them that they have been fooled" እንዳለው ቢሆንም ቅሉ ህዝቤ መቸም ሁሌ አይሞኝም፡፡
በማስረጊያነት እውነት ሁሌም ያሸንፋል የምትለዋን ያዙልኝ፡፡
የምሁራን ስደት በእስካሁኑ ይብቃ!
(ደርብ ተፈራ)
የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ባልደረባ እና የፓለቲካል ሳይንስ ምሩቅ)