Thursday, 3 August 2017

ትምህርትን እንደ ትውልድ ማደንዘዣ

(በደርብ ተፈራ)

ይሄ ትውልድ የማወቅ ፍላጎቱን የተቀማ ነው፡፡ የተማረ ሰው ክብር ሲያጣ መማር በራሱ ይረክሳል፡፡ በታዳጊ አገሮች ትምህርት እንጀራ ነው፡፡ በእነዚህ አገራት ለማወቅ ብቻ የሚማሩ ካሉ እነሱ ብፁዓን ናቸው፡፡ ቢቻል የሰው ልጅ ለአዕምሮው ምግብ የሆነውን እውቀት በሆዱ ባይቀይረው መልካም ነበር ባይሰበር፡፡ መቼ ይሆን ግን ከድህነት ተላቀን ለማወቅ የምንማር?

‹‹ተማር ልጄ ወገን ዘመድ ሀብት የለኝም ከጄ፤
ላልተማረ ሰው ቀኑ ጨለማ ነው፡፡››

     ‹‹ያልፍልኛል ብለህ ወጣትነትህን በትምህርት ዓለም ካሳለፍክ በኋላ ማለፉ ቀርቶ ጊዜው ሲያልፍብህ ምን ይሰማሀል?›› ያኔ ነው ላልተማረ ሰው ቀኑ ጨለማ ነው የሚለው የዘፈን እንጉርጉሮ ለተማረ ሰው ቀኑ ጨለማ ነው ተብሎ መቀየር ያለበት፡፡ በድሮ ጊዜ ‹‹ትምህርት መራራ ናት ፍሬዋ ግን ጣፋጭ ናት›› ይባል ነበር አሉ፡፡ አሁን አሁን ግን ተምረህ የድህነት ሰርቲፊኬት ይዘህ ቤትህ ትመለሳለህ፡፡ ትምህርትና ፍሬዋም እንደ ሬት ይመሩሀል፡፡ መተኪያ የሌለውን እድሜህን ለትምህርት ሰውተህ በስተመጨረሻ ሜዳ ላይ ስትወድቅና የእውቀት ኢንቨስትመንት ቦታ ስታጣ ምን ትላለህ? ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ እንደሚባለው ተመርቆ ስራ ማግኘት ቀላል የሚመስላቸው ጥቂቶች ብቻ  አይደሉም፡፡ ነገሩ ግን እጅጉን ከባድ ነው፡፡ በጣም ያስጨንቃል፡፡ ረፍትም ይነሳሀል፡፡  ከራስህ ጋር ጦርነት ውስጥ ትገባለህ፡፡


     እድለኛ ከሆንክና ዘመድ ካለህ ወደ አንዱ የመንግስት መስሪያ ቤት ወይም የልማት ድርጅት ሸጐጥ ትላለህ፡፡ ይህ ካልተሳካልህም  ወደ ግል ድርጅቶች ሰፈር ሁነኛ ሰው ካለህ ምንም አይጨንቅህም፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውስጥ ‹‹ዘመድ እንጅ ልምድ›› አይደለም የሚፈለገው፡፡ በብርሃን ፍጥነት ደምወዝተኛ ትሆናለህ፡፡ ዘመድ ሳይኖርህ እውቀትና ልምድ ቢኖርህ የትም አትደርስም፡፡ አልፎ አልፎ ሁሉንም ሰንሰለት መበጣጠስ የሚችሉ ብቃት ያላቸውን ሰዎች ግን አይጨምርም፡፡ የተወሰኑ መስሪያ ቤቶችም በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ አይካተቱም፡፡


     በዘመዶችህ ትግልና ውለታ መንግስት ቤት ከገባህና ብልጥ ሆነህ ሲጠሩህ አቤት ሲያዝዙህም ወዴት ካልክ ወድያውኑ ስልጣን ይሰጥሀል፡፡ በልማታዊ ዘፈን መጨፈር ትጀምራለህ፡፡ በአብዮታዊ ድሞክራሲም ፈርሰህ እንደገና ትገነባለህ፡፡ እኛ ስለማናውቃት ኢትዮጵያም ማውራትን ትለማመዳለህ፤ የፓርቲ ታማኝነትህና የፖለቲካ ቁርጠኝነትህ እየታየ በሂስ ግለ ሂስ መከራህን አይተህ ሂስህን በልማታዊ ድስኩር አወራርደህ እና በአብዮታዊ ድሞክራሲ ውጠህ አቋምህ ይታይና ታዛዥ ከሆንክ ከጥቃቅንና አነስተኛ የስልጣን ቦታህ ወደ መካከለኛው እርከን ቀስ እያለም ወደ ከፍተኛው የአመራር ደረጃ የሚያበቃህን ስንቅ ትይዛለህ፡፡ ምንም አይጭነቅህ ታዛዥ ስብዕና ካለህ በእኛ የፖለቲካ አሰራር ቢችሉ ጨረቃ ላይም ይልኩሀል፡፡


     በተለይ ደግሞ እነሱ የሚሉህን የምትል ከሆነ አንተ የቁርጥ ቀን ልጅ ነህና ቁርጥ እየበላህ ስለ ደቡብ ኮሪያ፣ ታይዋንና ሲንጋፖር የልማታዊ መንግስትነት ተሞክሮና ያንተ አገር ስለምትከተለው መንገድ ትክክለኛነት ምስኪን ዜጎችን ሳይወዱ በግዳቸው አዕምሯቸውን እየደፈርክ ፕሮፓጋንዳህንም እየጋትክ ፅድት ባለ መኪና ትንፈላሰሳለህ፣ በብዙ ካሬ ሜትር ላይ የተንጣለለ ቪላ ቤትም ይኖርሀል፡፡ አለም ተራ ነውና አንተም እንደ ዘመዶችህ የምትወዳቸው ቤተሰቦችና ዘመድ አዝማድ ሁሉ ከሥራ አጥነት ትታደጋለህ፡፡ ምድራዊ ገነትም ትፈጥርላቸዋለህ፡፡ አለፍ ሲልም ለጓደኞችህ ጓደኞች ሳይቀር መከታ ትሆናለህ፡፡ ግን ግን አንተ ደናቁርት ስለሆንክ አስተሳሰብህም በዛው ልክ የወረደ መሆኑን አትዘንጋ፤ ለተማረ መሀይም ጥሩ ምሳሌም ነህ፡፡ ከእውቀት ማነስ የተነሳም አስተሳሰብህ ሻግቷል፡፡


     የሰፊው ህዝብ ልጆች ጥራት በሌለው የት/ት ስርዓት እየመከኑ አንተ ልጆችህን ከፈለክ አውሮፓ ደስ ካላለህም አሜሪካ ልከህ በእውቀት ተኮትኩተው ያድጉልሀል፡፡ አይበለውና አንድ ቀን የምትመካበት ስርዓት ራሱን በራሱ ቢያጠፋ ወይንም ህዝባዊ እምቢተኝነት እና ቁጣ ገርስሶ ቢጥለው ሳትውል ሳታድር በጨረቃ አገሪቱን ለቀህ ወደ ውጭ ትፈረጥጣለህ፡፡ በባዕድ መሬትም አገር አማን በሆነበት ወቅት በዘረፍከው ገንዘብ ተንፈላሰህ የድሎት ኑሮ ትኖራለህ፡፡ የሰው ልጅ በጭንቅላቱ እንጅ በሆዱ አያስብም፡፡ ለሆድህ ኖረሀልና ከህሊና ፍርድ አታመልጥም፡፡ አንድ ቀን በስራህና በሰራኸው ስራ ትፀፀታለህ፡፡ የሰው አገር የሰው ነውና ዞረህ ዞረህ አገርህ ስለምትናፍቅህ ወደ እናት ኢትዮጵያ ለመምጣት ማሰብህም አይቀርም፡፡ ጭንቅላት ሆድ የሆነበት ህይወትህ ተቀይሮ ነፍስህ በጥያቄ እረፍት ታሳጣሀለች፡፡ የትውልድ ክፍተትም ፈጥረሀልና መጥፎ ውለታህ መቼም አይረሳልህም፡፡ አንተን ተከትለውም እልፍ አዕላፍ ወገኖች በተሳሳተ የህይወት መንገድ ተጉዘዋል፡፡


     ይህ ሁሉ የሚያመላክተው በትምህርት ዓለም ውስጥ እያለህ ግብህን ሳትመታ መቅረትህን ነው፡፡ የትምህርት ውጤት እውቀት፣ ክህሎትና መልካም ስነ ምግባር ናቸው ካልን አንተ ከእውቀት ነፃ፣ ክህሎትም ችሎታም የሌለህ ምግባረ ብልሹ ሰው ነህና የዘራኸውን ማጨድህ አይቀርም፤ መቼም አንድ ገበሬ ማሳው ላይ ጤፍ ዘርቶ እያለ መኸር ሲደርስ ከማሳው ስንዴ አያጭድም፡፡ እትብትህ የተቀበረባት አገርህና ከእለት ቁርሱና ጉርሱ ቀንሶ ያስተማረህ ህዝብም የህሊናህን ጥያቄ በቀላሉ እንዳትመልስ ያወሳስብብሀል፡፡ ከአገርህ ብሄራዊ ጥቅም አስበልጠህ ለግላዊ ጥቅምና ፍላጎትህ ባሪያ ሆነዋልና አንተ ለማንም አትጠቅምም፡፡ መሪ ማለት እኮ ትክክለኛውን መንገድ የሚያውቅ፣ መንገዱን ለሌሎች የሚያሳይ ብሎም በመንገዱ የሚሄድ ማለት ነው፡፡ አንተ ግን ትክክለኛውን መንገድ ሳታውቅ ሌሎችንም በስህተት ጎዳና አስገብተህ በተሳሳተው መንገድ ስትጓዝ ኖርክ፡፡ ይብላኝልህ! እርጅናውም መጣ ሞቱም አይቀርልህ፡፡ ባትወለድ ይሻል ነበር ከንቱ ሆነህ ተወልደህ ከንቱ ሆነህ ኖረህ በከንቱ አለፍክ፡፡ ያንተ መጨረሻ እንድግድህ ይሄ ነው፡፡


     ካምፓስ ላይ ቀልዳችሁ በስራው አለም ደግሞ የሚያግዛችሁ ዘመድ ከሌላችሁ ከሁለት የወጣ ጎመን ማለት ከናንተ ሌላ የለም፡፡ አንደኛ ከእውቀቱ ባህር አልጨለፋችሁም፡፡ ሁለተኛ በባሌም በቦሌም ብላችሁ ስራ ቢጤ አልያዛችሁም!፡፡ በዚህ የተነሳ ‹‹ሜዳ ላይ ቀረሁኝ›› አይነት ዜማ ድንገት በአዕምሯችሁ እየመጣ ይረብሻችኋል፡፡
     ሰለ ምረቃ ለማውሳት ያክል እንዳይደርስ የለምና የተማረ ሰው የነበረውንና ዛሬ ላይ የተነጠቀውን ቦታና ክብር አስታውሰህ ‹‹ከልኩ ላያልፍ›› በሚል የብስጭት ስሜት ምንም የህይወት ስንቅ ሳትይዝ የካምፓስ ቆይታህ ወደ መጠናቀቁ ተቃርቦ እውቀትን ሳትሸምት ጓደኞችህ ለምረቃ መፅሄት የሚሆን ጥቅስ (ላስት ወርድ) አፈላልግ ልንመረቅ ምናምን ቀን ቀረን ይሉሀል፡፡ ‹‹ሳይጨርሰኝ ጨረስኩት›› (‹‹ላልቅ ስል አለቀ››)፣ ‹‹መመረቅስ በፈጣሪ ነው››፣ ‹‹ምቀኛ ገና ምን አይተሸ››፣ ‹‹ይሄ ሁሉ ጣጣ ለአንድ ባርኔጣ…›› ወዘተ ከሚሉት ጥቅሶች አንዱን መርጠህ ሱፍህን ገጭ አድርገህ፤ ይህም አልበቃህ ብሎ የህዝብ አደራ መሸከምህን አመላካች የሆነውን ጥቁር ጋዋን አጥልቀህ የተነሳኸውን ፎቶ አንዱን ከጥቅሱ ጋር ለምረቃ መፅሄት ሌላውን ለቤተሰብ ብትልክላቸውና ግድግዳ ላይ ቢሰቅሉት ስትሞት ማልቀሻ ካልሆነ በስተቀር ሌላ ፋይዳ አይኖረውም፡፡


      ከትምህርት ተቋማት ሳንወጣ እስኪ ዩኒቨርስቲዎቻችንን ትንሽ እንማቸው፡፡  ዩኒቨርሲቲዎቻችን የመንደር ተቋማት ሆነዋል፡፡ ዩኒቨርስቲ ማለት ዩኒቨርስ ከሚለው ቃል ጋር የተያያዘ ስያሜ አለው ካልን አለም አቀር አድማስ ሊኖረው የሚገባ ተቋም ነው ብለን መውሰድ እንችላለን፡፡ ስለዚህ አደረጃጀቱና እንደ መማር ማስተማር፣ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት የመሳሰሉ ተልዕኮዎቹ አለም አቀፍ ይዘት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ የሰው ሀይል ስብስባቸውም በጎሳ ተዋፅኦ ሊሆን አይገባም፡፡


     ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ የምናገኘው እውነታ ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፕሬዚዳንቶች እና የቦርድ አባላት እንድሁም ዝቅተኛ የአስተዳደር ባለሙያዎች የአካባቢ ተወላጅ ተብየዎች ጥርቅም እየሆነ ነው፡፡ ሁሉም ዩኒቨርስቲዎች ባይባልም አብዛኞቹ የዚህ ችግር ሰለባ ናቸው፡፡ እንደ ማስተባበያ የሚቀርበውም ከተቆርቋሪነት ጋር የተያያዘ ምክንያት ነው፡፡
‹‹እኔ ከሰሜን ከመጣሁ ደቡብ ላይ ላለ ዩኒቨርስቲ ተቆርቋሪም ቆርቋሪም የማልሆንበት
ምክንያት ግን እስከዛሬ አልገባህ ብሎኛል፡፡››
      ይህ የመንደር አስተሳሰብና ጎጠኝነት ጉዳት አለው፡፡ ፀረ-ኢትዮጵያዊነት አካሄድም ነው፡፡ በተቋማቱ ውስጥ ብዝሃነት ሲኖር የተለያየ አመለካከት ይፈጠራል፡፡ ይህ የአመለካከት ልዩነት ነገሮችን ከብዙ አቅጣጫ እንድንረዳ ሲያግዘን የሃሳብ ፍጭቱ ደግሞ ለችግሮች የተሻለ መፍትሄ ለመሻት ይረዳል፡፡ አንድ ሰው ዩኒቨርስቲው ካለበት አካባቢ ስለተወለደ ሳይሆን ብቃቱ ታይቶ ነው አመራር ቦታ ላይ መቀመጥ ያለበት፡፡ የኦሮሞ ምሁር አማራ ዩኒቨርስቲዎች ላይ ባይተዋር ከሆነ የአማራ ምሁር ኦሮሞና ትግራይ ዩኒቨርስቲዎች ላይ ከተገፋ፣  የትግሬ ምሁር አማራና ኦሮሞ ዩኒቨርስቲዎች ላይ ቦታ የለህም ከተባለ፣ ደቡቡ ወደ ክልልህ ዩኒቨርስቲዎች ሂድ ከተባለ…ዩኒቨርስቲዎች አለም አቀፍ ተቋም መሆናቸው ቀርቶ በፌደራል መንግስት ስር መቋቋማቸውም ጥያቄ ያስነሳል፡፡ እውነት እላችኋለሁ ዩኒቨርስቲዎቻችን ላይ ትልቅ አደጋ ተጋርጧል፡፡ የመንደር ፖለቲካ የዬኒቨርስቲዎችን አጥር ጥሶ መግባቱን ስታውቁ እጅጉን ታዝናላችሁ፡፡


     በዩኒቨርስቲዎቻችን አካባቢ እየተፈጠረ ያለው ተመሳሳይ የሆነ የሰው ሃይል ስብስብ ከምክንያት ይልቅ ‹‹በእኔነትና በእነሱነት›› መመዘኛ ተቋሞች እንድመሩ ብሎም የባይተዋርነት ስሜት እንድነግስ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ መልካም አስተዳደር፣ ብልሹ አሰራርና ስርዓት አልበኝነትም በተቋማቱ ውስጥ ይነግሳሉ፡፡ ግልፅነት የተሞላበት አሰራር ይዳከማል፡፡ ውሳኔዎችም ሲተላለፉ ከህግና መመሪያ ይልቅ በግለሰቦች ፍላጎት ላይ ተመስርቶ እንድሆን አስቻይ ሁኔታዎች ይመቻቻሉ፡፡ ተቋማትም አለምአቀፋዊነት  ሳይሆን ሰፈርተኝነት መገለጫቸው  ይሆናል፡፡  በሌላ መልኩ ደግሞ በዩኒቨርስቲዎቻችን አካባቢ እንድሁም ታችኛውን የት/ት እርከን ጨምሮ የብዛት ወይም ተደራሽነት ችግሩ ላይ በማተኮር የጥራቱ ነገር ችላ የተባለ ይመስለኛል፡፡ ጥራት እንጅ ብዛት ለአገር አይጠቅምም፡፡ የቱ ይቅደም የሚለው ግን አድስ ተሰርቶ ያለቀ ቤት ዕቃ እስከሚሟላ ተዘግቶ ይቀመጥ ወይስ እንግባበትና ቀስ በቀስ እቃውን እናሟላ እንደማለት ነው፡፡ ምርጫውን ለእናንተ ትቻለሁ፡፡ በበኩሌ የያዝኩት አቋም ዩኒቨርስቲዎች አይስፋፉ፤ቁጥራቸው አይጨምር ማለት እንዳልሆነ ያዙልኝ፡፡ ግን ምርጫ በደረሰ ቁጥር የመሰረት ድንጋይ እየጣሉ ዩኒቨርስቲ ይገነባልሀል ማለት ቀበሌዎቻችንን ሳይቀር የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ባለቤት ለማድረግ ያሰቡ አስመሰለባቸው፡፡ እንደ አሸን የፈሉ ተቋማት ቢኖሩን አይከፋኝም፤ እኔን የሚያሳስበኝ የሰው ሀይልና የማቴሪያል አቅርቦት ሳይኖር ህንፃ ብቻ ቆሞ ሲቀር ስለታዘብኩ ነው፡፡ ከጥቂት አመታት በኋላ በነርስ የሚማሩ ዶክተሮች እና በድግሪ የሚማሩ ማስተርሶች ሊያጋጥሙን ቢችሉ ውርድ ከራሴ፡፡ ሳንማር እያስተማርን እስከመቼ? ተምረንም የተሻለ ተስፋ ሊኖረን አልቻለም፣ ስለዚህ ማንን እያየን እንማር?


     ‹‹አምሳ ቢወለድ አምሳ ነው ጉዱ ከተባረከ ይበቃል አንዱ›› በማለት በጣት የሚቆጠሩ ዜጎችን አስተምረን ኢትዮጵያን ለእነሱ ብቻ አደራ ሰጥተን ሌሎቻችን እጅና እግራችንን አጣጥፈን ብንቀመጥ ሽክማቸው እጅጉን የከበደ ነው የሚሆነው፤ አመንም አላመንም! ወደድንም ጠላንም አገር በተወሰኑ ግለሰቦች እና ቡድኖች ጥረት ብቻ ልትለማ አትችልም፡፡ ጥቂቶች የተለየ የመሪነት ችሎታ ካላቸው እስኪ ቀስቅሱልኝ ምሁሩ ይነሳ፤ ይከተል የለም ወይ ሌላው በዳበሳ እንደሚባለው ብዙሃኑ እነሱን እያየ ይከተል ይሆናል፡፡ ነገር ግን እነሱ የድህነት፣ ኋላ ቀርነት፣ አምባገነንነት፣ ኢ-ፍትሃዊነት እና ሌሎች የማህበረሰብ እድገት ማነቆዎችን ለመስበር ሲሞክሩ ሰፊው ህዝብ በእውቀትና ክህሎት ካላገዛቸው ልፋታቸው ፍሬ ሊያፈራ አይችልም፡፡ ስለዚህ የሰው አዕምሮ ላይ በሰፊው ኢንቨስት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ባይሆን ግን የሁላችንም ጐጆና መጠጊያ የሆነችው ኢትዮጵያ መፍረሷ እውነት ይሆናል፡፡ የዘመመችዋን ጐጆ ሊያቀናም ሊያፈርስም የሚችለው ህዝብ ነው፡፡ አጥፊዎችም በተናጠል ጐጆዋን ሲነቀንቁ ዝም ከተባሉ ያፈርሷታል፡፡


     ዩኒቨርሲቲዎችም ሲገነቡ ብቃት ያለው የሰው ሃይል፣ በቂ የመፅሃፍት አቅርቦት፣ደረጃውን የጠበቀ የቤተ-ሙከራ አደረጃጀትና ምቹ አካባቢያዊ ሁኔታ እና የመሳሰሉት ከግምት ውስጥ መግባት ይኖርባቸዋል እላለሁ፡፡ የአካዳሚክ ነፃነትም ሊታሰብበት ግድ ይላል፡፡ ይህ ካልሆነ የዘመመችው ጐጆ እንድትፈርስ መሰሶውን በመጋዝ መቁረጥ ነው፡፡
      ወደ መጀመሪያው ሀሳብ ስመልሳችሁ….በአድስ መንፈስና ወኔ ብሎም ለየት ባለ የስራ ፍቅር የትምህርት አመቱን አሀዱ ብየ ጀመርኩ፡፡ ስራውን በይፋ ጀምሬ ቆየትየት ስል ግን ያ ሁሉ ወኔና የስራ ፍቅር ድራሻባቱ ጠፋ፡፡ ለዚህ ምክንያት የሆነው ደግሞ ከተማሪዎች የትምህርት ፍላጎት ጋር የተያያዘ ችግር ነበር፡፡ ከእለታት አንድ ቀን ተማሪዎችን ምን ሆናችሁ ነው የማታነቡት ስላቸው! አንዱ ተማሪ ያው እኛኮ ጊዜ ለማሳለፍ እና ቤተሰቦቻችን ደስ እንድላቸው እንጅ ተምረን ያልፍልናል ብለን አይደለም የምንማረው ሲል  ተናገረ፡፡ በወቅቱ የተሰማኝን ስሜት መግለፅ ይከብደኛል፡፡ ለካ ድንጋይ ላይ ውሀ እያፈሰስኩ ነበር፡፡


     ለነገሩ ተማሪዎቹ ምን ያድርጉ? ፕሮፌሰር ሆኖ ኪራይ ቤት ሲኖር፣ ለማንበብ ሲነሳ ሰዓት አልፏል ብለው የመብራት ቆጣሪ ሲያጠፉበት እና ማንበብ እየፈለገ 500 ብር የሚሸጥ መፅሀፍ እንኳን መግዛት ሲያቅተው፤ ይህ ብቻ አይደለም አቅም ስለሌለው ‹‹በሰማይ ነው ቤቴ›› ብሎ ራሱን እያታለለ ቤት አልባ ምድራዊ ህይወት ሲኖር…ወዘተ እያዩ ተማሪዎች እንደት ይማሩ? ሳይማሩ እያስተማሩ ያሉ የኔ ቢጤ አስተማሪዎችም ራሳቸውን በእውቀት ይገነቡ ዘንድ ከመሰረታዊ ፍላጎት እስር ቤት መውጣት አለባቸው፡፡ እውነት ለመናገር ስለ ዕለት ጉርስህ እያሰብክ የተሻለ የአካዳሚክ ህይወት ሊኖርህ ፈፅሞ አይችልም፡፡ ‹‹ማን ያውጋ የነበረ፣ ማን ያርዳ የቀበረ ነውና›› እየነገርኩህ ያለሁት ስለምኖርበት የትምህርት አለም ነው፡፡ መርዶውንም ስነግርህ እውቀትን በተስፋ ጠቅልየ ስለቀበርኩ ነው፡፡ በቃ! ማን ያውጋ የነበረ ማን ያርዳ የቀበረ ማለት ይህ ነው፡፡
     ትውልዱ አቅም ሳያንሰው ሁኔታዎች ስላልተመቻቹለትና አርአያ የሚሆን አካል ስለሌለ ብቻ ከንቱ ሆኖ ሲቀር ማየት በጣም ያማል፡፡ አስተማሪም ከተማሪዎች በተወሰነ መልኩ እንኳን መሻል አለበት፡፡ ይህ ካልሆነ ማንን እያዩ ይማራሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ በኢኮኖሚ አቅማቸው ደካማነት ምክንያት መምህራን ለተማሪዎቹ አርአያ መሆን እየቻሉ አይደለም፡፡ መምህር እውቀት ኖሮት ቢሆን እንኳን ተማሪ ብራንድ ጫማ አድርጎ መምህር በሸበጥ ክላስ የሚገባ ከሆነ የሚፈጥረውን ስሜት አስቡት፡፡


     ‹‹ተማር ልጄ ወገን ዘመድ ሃብት የለኝም ከጄ›› ተብሎ እንዳልተዘፈነ ሁሉ ዛሬ መማር መመራመር ሳይሆን መማረር ሆነብን፡፡ ዛሬ ላይ ቀኑ ጨለማ የሆነው ለተማረው የማህበረሰባችን ክፍል ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ስለዚህ ማንን እያየን እንማር?

በማስረጊያነት ትምህርትን ለአገርና ለትውልድ እንዳይጠቅም ማድረግ ከታሪክ ተወቃሽነት በዘለለ ብሄራዊ ወንጀል መሆኑን ዛሬም ነገም እንናገራለን፡፡


No comments:

Post a Comment

የፖለቲካ ባህላችን

አየሽ እዚህ አገር ከንቱ ፍረጃ አለ፤ አማኝ ሁሉ አክራሪ፤ ሙስሊሙ አሸባሪ፤ ጉራጌ ቋጣሪ፡፡ ትግሬ ሁሉ ወያኔ፤ ወጣቱ ወመኔ፡፡ አማራው ነፍጠኛ ፤ ደርግ ሁሉ ግፈኛ፡፡ ናቸው እያስባለ ፤ ቁልቁል የሚነዳን ጭ...